ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብና ቀውስ ሀገሪቱን ወደ መበታተን እንዳያመራት ያሰጋል ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 20/2010)ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብና ቀውስ ሀገሪቱን ወደ መበታተን እንዳያመራት ያሰጋል ሲሉ አንድ የአውሮፓ ፓርላማ አባል ተናገሩ።

ፓርቹጋላዊቷ የአውሮፓ ፓርላማ አባል አና ጎመሽ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ግጭትና የሕወሃት አገዛዝ እየተከተለ ያለው አካሄድ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው በሀገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን ሊያውክ የሚችል ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አሜሪካና አውሮፓ የኢትዮጵያን ሕዝብ የዲሞክራሲ ጥማት ወደ ጎን በመተው በጸረ ሽብር ትግል ስም ከአገዛዙ ጋር ማበራቸው ሀገሪቱን ለዚህ ቀውስ እንዳበቃት ተናግረዋል።

የዚህ ውጤትም ሀገሪቱን ወደ መፈረካከስ ሊያመራት ነው ብለዋል።

በ1997 በተደረገው ምርጫ የአውሮፓ ፓርላማን በመወከል ታዛቢ የነበሩት አና ጎመሽ ከዛ ምርጫ በኋላ ለተፈጠረው የሰው ሕይወት መጥፋትና የምርጫ ስርቆት ተጠያቂ የሆነው ህወሃት ነው ብለዋል።

ከዛ በኋላ የተካሄዱት ምርጫዎችም ቢሆኑ ተቀባይነት የሌላቸውና አገዛዙ ሕጋዊ እውቅናና ዲሞክራሲያዊ መሰረት እንደሌለው ማረጋገጫዎች ናቸው ይላሉ።

ይህም ሆኖ ግን አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ለሀገሪቱ ችግር ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት እየሰጡ ያለው ድጋፍ እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ስለ ሀገሪቱ ባለስልጣናትም ሲናገሩ በቅርቡ ከስራቸው መልቀቂያ ያስገቡት በረከት ስምኦንን በ1997 ምርጫ ወቅት በቅርብ እንዳወቋቸው ገልጸዋል።

አና ጎመሽ አቶ በረከት ማለት ከመለስ ዜናዊ በኋላ ያለ እጅግ አደገኛና፣አድራጎቱ ሁሉ በተንኮል የተሞላ ግለሰብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከስልጣን መልቀቁንም አላምንም ምክንያቱም ከጀርባ ሆኖ ተንኮሉን እንደሚሸርብ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ብለዋል አና ጎመሽ።

ሁል ጊዜ በጥርጣሬ የምመለከተው ግለሰብ ቢኖር በረከት ስምኦን ነው በማለት በእርግጠኝነት ተናግረዋል ።

በረከት አሉ አና ጎመሽ በ1997 ምርጫ ወቅት ለደረሰው ሕይወት መጥፋት ዋና ተጠያቂ ነው።

ይባስ ብሎ ግን እሱ ላደረሰው እልቂት እኔንና የአውሮፓ ህብረትን ተጠያቂ ማድረጉን በግርምት አስታውሰዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን በተመለከተም አስተያየታቸውን ሲሰጡ የዚምባቡዌውን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ማጨታቸው ብዙም እንዳልገረማቸው ተናግረው ግለሰቡ በሕወሃት ውስጥ ካሉና በወንጀል ከሚጠየቁ ግለሰቦች አንዱ ነው ብለዋል።

ለአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራልነት መመደቡ በአውሮፓ ያሉ የድርጅቱን ሰራተኞችና ሌሎች አካላትን እጅግ ያሳሰበ ጉዳይ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያን በተመልከተ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም በሀገሪቱ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተነስተው የራሳቸውን የወደፊት እጣ ፋንታ ራሳቸው ሲወስኑ ነው ብለዋል።

ሌላ የውጭ ሃይል መጥቶ ሀገራቸው ውስጥ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብለው መጠበቅ የለባቸውም ብለዋል አና ጎመሽ።