(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 20/2010) በአቡነ ማትያስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የ14 ቀናት ጸሎተ ምህላ እንዲታወጅ ወሰነ።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች በመጥቀስ ስለሀገራችን ሰላምና የህዝብ አንድነት መጠበቅ ሲባል ጸሎተ ምህላው እንዲታወጅ መወሰኑን አስታውቋል።
ከመንግስት ጋርም በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ለመነጋገር በሲኖዶሱ በኩል ውሳኔ ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በመላ ሀገሪቱ የ14 ቀናት ጸሎተ ምህላ ይደረጋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶችና የደረሱት ጉዳቶች አሳዛኝ እንደሆኑ የመከረው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምህላውን እንዲያደርጉ ውሳኔ አስተላልፏል።
በወርሃ ጥቅምት የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባዔ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ መነጋገሩም ተጠቅሷል።
የህዝቡ ሰላምና አብሮት የኖረው አንድነት እንዲጠበቅ ቤተክርስቲያን የበኩሏን ሚና መወጣት እንደሚገባት የገለጸው የሲኖዶሱ ጉባዔ በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ውይይት ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል።
ከመንግስት ጋር ይደረጋል የተባለው ውይይት በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች ያልተጠቀሱ ሲሆን የታወጀው ጸሎተ ምህላ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም አልተገለጸም።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ጸሎተ ምህላው የሚጀመርበትን ቀን በመግለጪያ እንደሚያስታውቅ ሀራ ዘተዋህዶ የተሰኘ በቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ድረ ገጽ ጠቁሟል።
የቅዱስ ሴኖዶሱ ጉባዔ በየአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግም ውሳኔ ላይ ደርሷል። ቤተክርስቲያኒቷ ለህዝብ አለኝታነቷን የምታሳይበትን የገንዘብና ሰብዓዊ ረድዔት ለማድረግ ተወስኗል ያለው ምልዐተ ጉባዔው የቤተክርስቲያኒቱን ድጋፍ በሚመለከተው አካል በኩል እንዲደርስ መታዘዙንም አስታውቋል።
በአቡነ መርቆርዮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ በህዳር ወር መጀመሪያ በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት በሚያደርገው ጉባዔ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንደሚመክር ማስታወቁ ይታወሳል።
የኦሃዮው ጉባዔ በዋና አጀንዳነትም በኢትዮጵያ የእርቅና ሰላም ጉዳይ ላይ ምክክር እንደሚያደርግ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለኢሳት በላከው መግለጪያ ላይ ተጠቅሷል።