(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 14/2010)ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ተላላፊ ያለሆኑ በሽታዎች የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው ከሾሙ በኋላ ያነሱበት ሂደት እንዲጣራ የተባበሩት መንግስታት ጉዳይ ተመልካች ድርጅት ጠየቀ።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተመልካች ድርጅቱ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጉዳዩን ተመልክተው ሹመቱን ቢያነሱም ሞራለቢስ ውሳኔያቸው ግን ሊመረመር ይገባል ብሏል።
ሮበርት ሙጋቤ በአለም ጤና ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የበጎ ፈቃድ አምባሳደር እንዲሆኑ በዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሲወሰን የምዕራብ ሀገራትና ታዋቂ የአለማችን ሰዎች ከፍተኛ ድንጋጤ ነበር የተሰማቸው።–ሮበርት ሙጋቤ ሰብአዊ መብትን የሚጥሱና የዲሞክራሲ ጠላት ናቸው በሚል።
ይህንኑ መረር ያለ ተቃውሞ ካሰሙት መካከል የአለም ጤና ድርጅት ዋነኛ የፋይናንስ ደጋፊ የሆኑት እንግሊዝና አሜሪካ ይገኙበታል።
በአለም ዙሪያ ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረው የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሙጋቤን የመሾም ጉዳይ እንደገና እንዲታይና ውሳኔውም እንዲቀለበስ አስጠይቋል።
የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምም ቅሬታቸውን ተቀብያለሁ በሚል ሹመቱን ማንሳታቸውን ወዲያውኑ አሳውቀዋል።
ይህ ከሆነ በኋላ ግን መንግስታዊ ያልሆነው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተመልካች ቡድን ውሳኔውን መቀልበሳቸው አዎንታዊ ቢሆንም ሂደቱ ግን እንደገና ሊመረመር ይገባል ሲል ጥያቄ አቅርቧል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሒለል ኒዬር ሮበርት ሙጋቤ በሀገራቸው ዲሞክራሲን የመጨፍለቁና የጤና ተደራሽነትም እንዳይኖር ያደረጉ ናቸውና ብለዋል።
እናም ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ውሳኔያቸው ችግር ያለበትና ብቃታቸውም ስለሚያጠራጥር ጉዳዩ እንደገና መመርመር አለበት ነው ያሉት።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው በፊት ራሳቸው የዲሞክራሲ ጠላት ናቸው፣በሰዎች ግድያም ራሳቸው በአመራርነት ላይ የነበሩበት የሕወሃት ድርጅት ተጠያቂ ነው በሚል በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ሲቀርብባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ብቃታቸው ጥያቄ የሚያስከትል እንደሆነ በኢትዮጵያ የሰሯቸውን ስህተቶች በመጥቀስ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ነበር።
ያኔ ስለርሳቸው የሚቀርበውን አቤቱታ ችላ ሲሉ የነበሩት የተባበሩት መንግስታት ተቋማትና የምዕራባውያን ሀገራት አሁን ግን ሁኔታው ገብቷቸው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሊጠየቁ ይገባል ማለት ጀምረዋል።