(ኢሳት ዜና –ጥቅምት 13/2010)የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን እንዲለቁ ዓለም ዓቀፍ ግፊት እየተደረገ ነው።
ዶ/ር ቴዎድሮስ የዚምባቡዌውን ፕሬዝዳን ሮበርት ሙጋቤን የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርገው መሾማቸውን ተከትሎ በመላው ዓለም ቁጣ ተቀስቅሷል።
ዶ/ር ቴድሮስ ወዲያውኑ ሹመቱን በመሰረዝ የመጣባቸውን ተቃውሞ ሊያበርዱ ቢሞክሩም ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቀው ዓለም ዓቀፍ ግፊት ግን መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተሩ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ዓመት ያልሞላው ስልጣናቸው ጥያቄ ተነስቶበታል።
የዚምባቡዌውን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን የድርጅቱ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር እንዲሆኑ መምረጣቸው ያስነሳው ተቃውሞ የስልጣን መንበራቸውን መነቅነቁ እየተነገረ ነው።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ሮበርት ሙጋቤን በበጎ ፍቃድ አምባሳደርነት መምረጣቸውንና ፕሬዝዳንቱም መቀበላቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው ሀሙስ ነበር።
ይህ ውሳኔያቸው ከተሰማ በኋላ በመላው ዓለም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት አግኝቷል።
በቲውተር፣ በፌስቡክና በሌሎች የማህበራዊ የሚዲያ መድረኮች የተቀጣጠለው ተቃውሞ ለዶ/ር ቴድሮስ አስደንጋጭ እንደሆነባቸው ይነገራል።
ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ ወዲያኑ በቲውተር በጻፉት ምላሽ ጉዳዩን መልሰው እንደሚመለከቱት ገልጸዋል። ዛሬ ለፕሬዝዳንት ሙጋቤ የሰጡትን ሹመት መሻራቸውንም አስታውቀዋል።
ድ/ር ቴድሮስ የሰጡትን ሹመት በአራተኛው ቀን ሲሽሩት ፕሬዝዳንት ሙጋቤን አማክረው እንደሆነም ተገልጿል።
በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወነጀሉትን ሰው ለበጎ ፍቃድ አምባሳደርነት ሾመዋል በሚል ከታላላቅ ሰዎች፣ ከዲፕሎማቶች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የተነሳው ተቃውሞ በመጨረሻም ስልጣን እንዲለቁ ወደሚጠይቅ ዘመቻ ተቀይሯል።
በተለይ ዓለም ዓቀፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጥምረት የሙጋቤ ሹመት ክፉኛ እንዳስደነገጠው መግለጫ በማውጣት አስታውቋል።
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዎችም ‘’አሳፋሪ’’ ሲል የዶ/ር ቴድሮስን ውሳኔ ተቃውሞታል።
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅትን መሰረታዊ እሴትና መመሪያ የማያውቁ ከሆነ ድርጅቱን የመምራት አቅም የላቸውም የሚለው ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለማብረድ የሙጋቤን ሹመት መሻራቸውን የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የፖለቲካ ሰዎችን በዓለም ጤና ድርጅት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ለማድረግ በሚል የወሰዱት ርምጃ መሆኑን እየገለጹ ናቸው።
ሆኖም የሙጋቤን ሹመት ካነሱም በኋላ ተቃውሞው እንዳልተቋረጠ መረጃዎች ያሳያሉ።
በቲውተር በተከፈተው ዘመቻ ዶ/ር ቴድሮስ ስልጣን እንዲለቁ ተጠይቋል።
ዘመቻውን ታላላቅ ሰዎች እየተቀላቀሉት ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ቦርድ ለድርጅቱ ክብር ሲል ዶ/ር ቴድሮስን ከስልጣን እንዲነሱ እንዲያደርግ የሚጠይቅ አቤቱታ ቀርቧል።
ወደ ዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነተ የመጡበት ውድድር ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበባቸው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ወንበራቸውን በቅጡ ሳይዙ የተከፈተባቸው ዘመቻ ምን ሊያመጣ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው።
በሰብዓዊ መብት ጥሰት ክፉኛ የሚብጠለጠለው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሰው ዳይሬክተር ሲሆኑ ያልተቃወሙ ወገኖች በሙጋቤ መሾም መቆጣታቸው ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉ አንዳንድ ታዛቢዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከስልጣን ይልቀቁ በሚል ስለተከፈተባቸው ዘመቻ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም።