(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 13/2010) ናይጄሪያ ውስጥ ሶስት ሴቶች በሰውነታቸው ላይ በተጠመደ ቦንብ ባደረሱት ፍንዳታ 13 ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሰዎች ቆሰሉ።
የሀገሪቱ ጦር ቦኮ ሃራም የተባለው አክራሪ ቡድን ሊደመሰስ ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቶታል እያለ በሚናገርበት ወቅት የተፈጸመ ከባድ ጥቃት መሆኑም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሶማሊያ ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ አቅራቢያ በደረሰ የመንገድ ዳር ፍንዳታ 11 ሰዎች መሞታቸው አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል።
በናይጄሪያ እሁድ እለት የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ የሀገሪቱ ጦር ቦኮ ሀራም የተባለው የእስልምና አክራሪ ቡድን ሊደመሰስ ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው የቀረው በሚል መግለጫ እየሰጠ ባለበት ወቅት ሲፈጸም ከወራቶች በኋላ የተፈጸመ ከባዱ ጥቃት እንደሆነ እየተዘገበ ነው።
ፍንዳታው በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ሜይድጉሪ ግዛት ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ይህም አካባቢ ከቻድ ሃይቅ ጋር የሚዋሰንና የቦኮ ሀራም ቡድን እስላማዊ መንግስት ለመፍጠር ላለፉት 9 አመታት የትጥቅ ትግል እያካሄደ የሚገኝበት አካባቢ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ይህም ግጭት እስካሁን 20 ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የመጀመሪያው ፍንዳታ ነዋሪዎች ለእራት የሚሆን ምግባቸውን በሚገዙበት ምግብ ቤት ሲፈጸም ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁለቱ ፍንዳታዎች ተከትለው 16 ያህል ሰዎችን አቁስለዋል።
ለጥቃቱ ወዲያውኑ ሃላፊነትን የወሰደ አካል ባይኖርም ከፍንዳታው ጥቂት ሰአታት በፊት ግን በርካታ የቦኮ ሀራም ታጣቂዎች ከከተማዋ አቅራቢያ ታይተው እንደነበር የኤ ኤፍ ፒ ሪፖርት አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አርብ ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ ሰዎች ላይና ተፈናቃዮች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እጅግ እንዳሳሰበው ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶማሊያ ቢያንስ 358 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው የቦምብ ጥቃት ሳምንት ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ አቅራቢያ በምትገኝና የእስልምና አክራሪዎች በሚበዙበት አካባቢ በደረሰ የመንገድ ዳር ፍንዳታ 11 ሰዎች መሞታቸው አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል።
ከሞቃዲሾ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለች መንደር በሚኒ ባስ ተጭነው በሚጓዙ ሰዎች ላይ በደረሰው በዚህ ጥቃት ሕይወታቸውን ካጡት አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል።
እንደ አልጀዚራ መረጃ ከሆነ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰአት አንድ ወታደራዊ ተሽከርካሪ በአካባቢው መታየቱንና ጥቃቱ አነጣጥሮ የነበረው በወታደራዊ ተሽከርካሪው ላይ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ሳምንት በደረሰውና የ358 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው፣ሌሎች 400 የሚሆኑ ሰዎች በቆሰሉበት እንዲሁም 50 የሚሆኑ የደረሱበት ባልታወቀበት ፍንዳታ የሞቱ ሁለት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሰዎች እንደሚገኙበትም ታውቋል።
አህመድ ኢዬውና መሀሙድ ኤልሚ የተባሉት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ሶማሊያውያን በሀገራቸው መልሶ ግንባታ ለመሳተፍና ሀገራቸውን ለማገልገል ወደ ሶማሊያ ተመልሰው መኖር ጀምረው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።