(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 13/2010)በኢትዮጵያ በውድቀት አፋፍ ላይ ያለውን አምባገነን የሕወሃት አገዛዝ ለማስወገድ ሁሉም የለውጥ ሃይሎች በጋራ እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ጥሪ አቀረበ።
ንቅናቄው በአሜሪካ ቨርጂኒያ ያካሄደውን የጥምር ድርጅቶቹን ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በኢትዮጵያ ሕዝቡ የሚፈልገውን ለውጥና ሕጋዊ ስርአት እውን ለማድረግ ሁሉም የለውጥ አካላት ሊተባበሩ ይገባል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ምክር ቤት መግለጫ ሀገሪቱ ወደ አስከፊ ቀውስ ከመግባቷ በፊት የለውጥ ሃይሎች ቀድመን ልንደርስ ይገባል ሲልም አሳስቧል።
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሆኑን መረዳቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የተወካዮች ምክር ቤት መግለጫ ያሳስባል።
ይህ ደግሞ የሕዝቡ ትግል እየተቀጣጠለ በመምጣቱ አገዛዙ ይህንኑ ለማፈን በሚያደርገው ሕገወጥ እርምጃ ነው ባይ ናቸው የንቅናቄው ምክር ቤትን መግለጫ ያወጡት አመራር አባላት።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የተወካዮች ምክር ቤት ተባባሪ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ፣ የስራ አስፈጻሚ አባሉ ዶክተር ዲማ ነገዎ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት ትግሉን አቅጣጫ አስይዞ ለመምራት የሚያስችል አደረጃጀት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።–አቶ ሌንጮ ለታ የንቅናቄው ተባባሪ ሊቀመንበር።
ዶክተር ዲማ ነገዎ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ በአቅምና በድጋፍ እራሱን ሲያጠናክር መቆየቱንም ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የተወካዮች ምክር ቤት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 20 እስከ 22/2017 ባካሄደው ስብሰባ ላይ ባወጣው መግለጫ በውድቀት አፋፍ ላይ ያለውን አምባገነን የሕወሃት አገዛዝ ለማስወገድ ሁሉም የለውጥ ሃይል በጋራ ሊቆም ይገባል ብሏል።
በኢትዮጵያ ፍትህ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነበት ሕጋዊ ስርአት እውን ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነውም ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ተወካዮች ምክርቤት በኢሉባቦር፣በዲጋና ጮራ ወረዳዎች ብሔርን ከብሔር በማጋጨት የተካሄደውን ግድያ አውግዟል።
ይህ ግድያ የተቀነባበረው በሕወሃት ጉዳይ ፈጻሚዎች ነው ሲሉ አቶ ሌንጮ ለታ ድርጊቱን አውግዘዋል።