(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 7/2010)በሶማሊያ ሞቃዲሾ የደረሰውን ዘግናኝ የሽብር ፍጅት ተከትሎ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰለባዎቹን ለመታደግ መንቀሳቀስ ጀመረ።
ወደ 300 ሰዎች ያለቁበትንና ከ300 በላይ የቆሰሉበትን ይህንን የቅዳሜውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካና የኳታር አውሮፕላኖች መድሃኒት ጭነው ሞቃዲሾ አርፈዋል።
ቱርክ ከቆሰሉት ውስጥ 40 የሚሆኑትን ለህክምና ወደ ሃገሯ ስትወስድ ጎረቤት ጅቡቲን ጨምሮ ሀገራት ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ሕዝብ በሚበዛበት ሆቴልና የመንግስት ሕንጻዎች ባሉበት የሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በጭነት መኪና ላይ በተጠመደ የፈንጂ ጥቃት የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አብዱራህማን ኡስማን እንደገለጹት 281 ሰዎች ሞተዋል።
ይህ የተረጋገጠ የሟቾች ቁጥር ሲሆን ከ100 በላይ ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።
በአደጋው ያለቁትን ሰዎች ማንነት ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑም ማንነታቸው ያልታወቀውን የ165 ሰዎች የቀብር ስነስርአትም ሰኞ በአንድ ላይ መፈጸሙንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ከሟቾቹ ውስጥ በዚህ ሳምንት የህክምና ትምህርቷን የምትጨርስ ተመራቂ ወጣት እንደምትገኝበትም ታውቋል።
በሞቃዲሾ አካባቢ መቃብር በመቆፈር የሚተዳደረው መሀመድ ሀሰን ለአልጀዚራ እንደተናገረው የዚህ አይነት እልቂት የእርስ በርስ ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት እንኳን አልተፈጸመም።
በቀን ቢበዛ የሁለት ሰዎች መቃብር ይቆፍር እንደነበር የገለጸው መሀመድ ሀሰን ቅዳሜ ዕለት ስራ ጨርሰው መቃብር ቦታውን ሲለቁ ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን ያስታውሳል።
ይህም ስራ እንደሚበዛብን ምልክት የሰጠን ቢሆንም በዚህ አይነት ያለፋታ በመቃብር ቁፋሮ እንጠመዳለን ብለን አልገመትንም ያለው የ50 አመቱ ጎልማሳ መሀመድ ሀሰን እሱ ብቻ የ17 ሰዎች መቃብር መቆፈሩን በመግለጽ የአደጋውን ስፋት ገልጿል።
በቃብር መቆፈር የዘወትር ስራዬ በመሆኑ በፊት የተለየ ስሜት አይሰማኝም ነበር።አሁን ግን ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ እንባዬ ፈሰሰ ሲል አልጀዚራ ተናግሯል።
አለም አቀፉ ማህበረሰብም የአደጋውን ሰልባዎች ለመታደግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል።
ወደ 300 ሰዎች ያለቁበትንና ከ300 በላይ የቆሰሉበትን ይህንን የቅዳሜውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካና የኳታር አውሮፕላኖች መድሃኒት ጭነው ሞቃዲሾ አርፈዋል።
ቱርክ ከቆሰሉት ውስጥ 40 የሚሆኑትን ለህክምና ወደ ሃገሯ ስትወስድ ጎረቤት ጅቡቲን ጨምሮ ሀገራት ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።