(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 6/2010) የዛሬ ሁለት ሳምንት የተጀመረው የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ በተፈጠረበት የቴክኒክ ችግር ምክንያት መራዘሙ ታወቀ።
ባለፉት 13 ቀናት ያመለከቱ አመልካቾች የቀደመው ውድቅ በመሆኑ እንደገና ማመልከት እንዳለባቸውም በየሀገሩ ባሉ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 3/2017 እስከ ህዳር 7/2017 መርሃ ግብር የተያዘለት የ2019 የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ በኮምፒዩተር ስርአቱ ላይ በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ላለፉት 13 ቀናት የገቡት ማመልከቻዎች ውድቅ ሆነዋል።
አንድ ሰው ከአንድ ግዜ በላይ ማመልከቻ ካቀረበ ወዲያውኑ ከውድድሩ ውጭ እንደሚሆን የታወቀ ቢሆንም ባለፉት 13 ቀናት ማመልከቻ ያቀረቡት ግን በድጋሚ ማመልከት እንደሚችሉ ተመልክቷል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት የዲቪ ማመልከቻው ከፊታችን ረቡዕ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 18/2017 ተጀምሮ እስከ ህዳር 22/2017 እንደሚቀጥልም ታውቋል።
የቀድሞው ቀነ ገደብ ህዳር 7 እንደነበር ይታወሳል።