(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 6/2010) እኔ ብፈታም ሀገሪቱ ግን እስር ቤት ውስጥ ናት ሲል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ገለጸ።
በሶስት ዓመት የእስር ቤት ቆይታው ስለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳላገኘ ጋዜጠኛ ተመስገን ከኢሳት ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
ትላንት ከእስር የተለቀቀው ጋዜጠኛ ተመስገን በእስር ቤት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሌላ የሚፈቀድ ሚዲያ ባለመኖሩ በሀገሪቱ ስለተከሰቱ ነገሮች መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ ተናግሯል።
ጋዜጠኛ ተመስገን በቀጣይም ህክምናው ላይ እንደሚያተኩር አስታውቋል።
በሶስት ዓመታት 41 ክሶች ቀርበውበታል። ከዛ በኋላም ክሶቹ መቆሚያ አልነበራቸውም። ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ክሶች ፋይል እንደተከፈተበት የሰማው በሬዲዮ ነው።
በ2004 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ፍትህ የተሰኘው ጋዜጣ ሲዘጋና ከ30ሺህ ኮፒዎች በላይ በፖሊስ ሲወሰድ ጀምሮ ፍርድ ቤት በመመላለስ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይቷል።
በመጨረሻም ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን በማሰራጨትና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በአመጽ ለመናድ የሚገፋፉ መረጃዎችን በማውጣት በሚሉ ክሶች የሶስት ዓመት እስር ተበይኖበት ወደ ወህኒ ገብቷል- ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ።
ምክንያቱ ሳይታወቅ የአመክሮ መብቱ ከተነፈገ በኋላ በእስር የቆየው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፡ የእስር ጊዜውን አጠናቆ ባለፈው አርብ ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ በዕለቱ አለመፈታቱ ታውቋል።
ትላንት ዕሁድ ጥቅምት 5/2017 ከሶስት ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላም መፈታቱን ለማወቅ ተችሏል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በእስር ቤት ቆይታው በተደጋጋሚ ህክምና መነፈጉን የጠቀሱት ቤተሰቦቹ ህይወቱ አደጋ ላይ መውደቁን በመጥቀስ አቤቱታ ሲያቀርቡ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በጆሮና በጀርባ ህመም የሚሰቃየው ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ የቅድሚያ ትኩረቱ ለህክምና እንደሚሆን በተለይ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
የእስር ቤት ቆይታውን በተመለከተ የተናገረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፡ ከሶስት ዓመት ውስጥ ሁለቱን አመት ያሳለፈው በጨለማ እስር ቤት ውስጥ ነው። ምንም መረጃ አያገኝም። መጻህፍት ተከልክሏል።
ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውጭ የሚመለከተው መገናኛ ብዙሃን አልነበረም። እናም ከሶስት ዓመት በፊት ስለነበረው እንጂ ከዚያን ወዲህ ስላለው የሀገሪቱ ሁኔታ መረጃው እንደሌለው ጋዜጠኛ ተመስገን ይናገራል።
ከእስር ተለቆ ከወላጅ እናቱና ከቤተሰቦቹ ጋር የተገናኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለህክምናው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው ገልጿል።
ስታሰርም ነጻ ነበርኩ ስፈታም ነጻ ነኝ ያለው ጋዜጠኛ ተመስገን እኔ ብፈታም ሀገሪቱ ግን አሁንም እስር ቤት ውስጥ ናት ሲል ተናግሯል።