(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 3/2010)በላይቤሪያ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የቀድሞው ዝነኛ የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ በከፍተኛ ውጤት በመምራት ላይ መሆኑ ታወቀ።
ቆጠራ ከተጠናቀቀባቸው 15 ምርጫ ጣቢያዎች በአስራአንዱ ጆርጅ ዊሃ ሲያሸንፍ የቅርብ ተቀናቃኙ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጆሴፍ ቦኪ አንድ ምርጫ ጣቢያ ብቻ በማሸነፍ እየተከተሉት ይገኛሉ።
አጠቃላይ የምርጫው ውጤቱ ሳይታወቅና አሸናፊነቱ ሳይረጋገጥ ለጆርጅ ዊሃ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ያስተላለፉት የቀድሞው የኳስ አሰልጣኙ አርሴን ዌንገር ትችቶችን አስተናግደዋል።
የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዝዳንትና በአሁኑ ወቅት የ50 አመታት እስራት ተፈርዶባቸው በብሪታኒያ ወህኒ ቤት የሚገኙት ቻርለስ ቴይለር በምርጫው ሒደት ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ እያደረጉ መሆናቸውም ታውቋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤቱን ሳያሳውቅ ጆርጅ ዊሃ አሸንፏል በማለት ደስታቸውን የገለጹት የአርሴናሉ ዋና አሰልጣኝ አርሴን ዌንገር ባልተገለጸና ተቆጥሮ ባልተጠናቀቀ ውጤት መልዕክት ለጆርጅ ዊሃ በማስተላለፋቸው የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆነዋል።–ትችቶችም ቀርበውባቸዋል።
በአንድ ወቅት በአለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የአመቱ ምርጥ ተጫዋች በሚል የአለም የኳስ ቁንጮ እስከመባል የደረሰውና ይህንን ስያሜም ሲያገኝ በአፍሪካ ብቸኛ ሆኖ ዘልቋል።
ጆርጅ ዊሃ በአፍሪካም ሆነ በአለም ታሪክ ውስጥ ከኳስ ተጫዋችነት ወደ ሀገር መሪነት ጉዞ በማድረግም እየተጠቀሰ ይገኛል።
ለ73 አመታት አምባገነኖችን ስታፈራርቅ የቆየችውና በጠመንጃ ሹምሽር ውስጥ የዘለቀችው ላይቤሪያ ከ12 አመት በፊት በዲሞክራሲ ምርጫ መሪዋን መርጣለች።
በላይቤሪያ ታሪክ የመጀመሪያዋና በምርጫ የመሪነትን ስልጣን የጨበጡት ኤለን ጆንሰን ሰር ሊፍ በላይቤሪያም ሆነ በጥቅል አፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ወይንም የሀገር መሪ ሆነው ተመዝግበዋል።
በእርግጥ በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ንግስት ዘውዲቱ የሀገር መሪ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።
ኤለን ጆንሰን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ እንስትና በአለም አቀፍ ተቋማት የሰሩ ሀርቫርድን በመሳሰሉ ታላላቅ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የተማሩ ቢሆኑም በ12 አመት የስልጣን ዘመናቸው የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል አልቻሉም።
መሰረታዊ ፍላጎቶችንም አላሟሉም የሚሉ ወቀሳዎችም ይቀርቡባቸዋል።
እንዲያውም አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ላይቤሪያዊ ከዛሬ ይልቅ የጥይት ድምጽ እንሰማበት በነበረበት ጊዜ የተሻለ ኑሮ ነበር ማለቱም ተመልክቷል።
ጆርጅ ዊሃ የቀድሞውን የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት የእስረኛውን የቻርለስ ቴይለርን የቀድሞ ባለቤት ጄዊል ሀዋርድ ቴይለርን በምክትል ፕሬዝዳንትነት መያዛቸው የሕዝቡን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም እየተገለጸ ይገኛል።
ቻርለስ ቴይለርም ከታሰሩበት የብሪታኒያው ዱርሃም ወህኒ ቤት ስልክ በመደወል በምርጫው ሂደት ላይ ተጽእኖ እያደረጉ መሆናቸውም ተዘግቧል።
በ51 አመቱ ጆርጅ ዊሃና ስሊፒ ጆ ወይንም እንቅልፋሙ ጆሴፍ በሚልዋቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጆሴፍ ቦኪ መካከል ያለው ፉክክር ወደ መጨረሻ ምዕራፍ የተጠጋ ቢሆንም ከምርጫ ኮሚሽኑ የመጨረሻው ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል።
በሕዝባዊ መድረኮች ብዙውን ጊዜ ሲያንቀላፉ በመታየታቸው እንቅልፋሙ ጆሴፍ የሚል ስያሜ ያተረፉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጆሴፍ ቦኪ እያንቀላፋሁ ሳይሆን እያለምኩ ነው በማለት ድርጊቱን ለማስተባበል ሞክረዋል።
ከምርጫው ውጤት ማየት እንደተቻለው ግን ላይቤሪያውያኑ ሚኒስትር ጆሴፍ የነገሯቸውን ሳይሆን ያዩትን ያመኑ መስለዋል።
በመሆኑም ጆርጅ ዊሃ ወደ ፕሬዝዳንትነት መንበሩ ተጠግቷል።