(ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010) የደቡብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደኢህዴን በትግራይ ክልል ትምህርት ቤት አስገንብቶ ማስረከቡ ተሰማ።
ለትምህርት ቤቱ ግንባታ 12 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉም ታውቋል።
በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሊቀመንበርነት የሚመራው የደቡብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ንቅናቄ/ደኢህዴን የተመሰረተበት ጊዜና ቦታ በፓርቲው እራሱ ስምምነት ያለ አይመስልም።
አንዴ ከደርግ ውድቀት በፊት የስምጥ ሸለቆ ንቅናቄ በሚል ደቡብ ውስጥ ተመሰረተ።ሌላ ጊዜ ደግሞ በትግራይ ክልል ተቋቋመ በሚል የተምታታ ታሪክ ነው የሚነገረው።
ተመሰረተ የሚባልበት ጊዜ እራሱ በውል አይታወቅም።
ሲያሻቸው በ1985 ሲፈልጉ ደግሞ ሕገመንግስቱ በጸደቀበት 1987 ተመሰረተ በሚል የፓርቲውን እድሜ ከፍና ዝቅ ሲያደርጉት ቆይተዋል።
ሰሞኑን ደኢህዴን በትግራይ ክልል ድርጅቱ እንደተፈጠረ ተደርጎ ለመታሰቢያ እራሱ ያሰራው ትምህርት ቤት በ12 ሚሊየን ብር ወጪ ተገንብቶ ተመርቋል።
በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን ታህታይ ቆራሮ ወረዳ ደኢህዴን የተመሰረተበት ነው መባሉ ብዙዎቹን የሚያስገርም ነው። –ይህ ታሪክ በፊት ያልተሰማና ያልተነገረ በመሆኑ።
የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ግን ትምህርት ቤቱ በዚሁ አካባቢ የተገነባው የትግራይ ሕዝብ የደቡብ ታጋዮችን እቅፍ ድግፍ አድርጎ በጉያው ይዞ ያታገለን በመሆኑ ነው ይላሉ።
እናም 12 ሚሊየን ብር ወጭ አድርገን ለዚህ ቅንና በጎ ህዝብ ትምህርት ቤት ሰርተንለታል ብለዋል።
የደኢህዴኑ የፖለቲካ ሃላፊ ይህን ሲሉ ግን በደቡብ ክልል በድህነት የሚኖረውንና በየጫካው ያለትምህርትና ጤና ተቋማት ያለውን ሕዝባቸው በመዘንጋት ነው።
ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በትግራይ ያለው የትምህርት ሽፋንና በደቡብ ያለው የትምህርት ሽፋን የሰማይና የመሬት ያህል ልዩነት አለው።