(ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010) በ110 የጭነት መኪናዎች ተጭኖ ወደ ኬንያ ሊገባ የነበረው 44 ሺ ኩንታል ስኳር ከ2 ወራት የሞያሌ ቆይታ በኋላ ለብልሽት ተዳርጎ ወደ ወንጂ በመመለስ ላይ መሆኑ ተነገረ።
እስካሁን 44 የጭነት መኪናዎች ስኳሩን እንደጫኑ ናዝሬት ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ስኳሩን ዱባይ ለሚገኘው አግሪ ኮሞዲቲ የተባለ ኩባንያ የሸጠው በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የስኳር እጥረት ባለበት ሁኔታ ነው።
ስኳሩን ኬንያ ለማድረስ ተዋውሎ ሞያሌ ድረስ አጓጉዞ የነበረው ብራይት ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት ማህበር ስኳር ኮርፖሬሽንን ኪሳራ ሊጠይቅ መሆኑ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በአንድ በኩል በውድ ዋጋ የሀገር ውስጥ የስኳር እጥረቱን ለመሸፈን ከውጭ ምርቱን በብዛት ያስገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ውስጥ የተመረተውን ስኳር በኬንያ ድንበር ተሻግሮ ለዱባይ ኩባንያ መሸጡም ብዙዎችን አስገርሟል።
44ሺ ኩንታል ስኳር በ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የሸጠው ስኳር ኮርፖሬሽን ምርቱን ወደ ኬንያ እንዲሻገር የጫነው ምንም ገንዘብ ሳይከፈለው መሆኑ ደግሞ ችግሩን የባሰ አድርጎታል።
በ110 የጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ወደ ኬንያ ሊሻገር ሲል ሞያሌ ላይ እንዲቆም የተደረገው የኢትዮጵያ ስኳር ላለፉት 2 ወራት ጸሃይና ቁር እየተፈራረቁበት ለብልሽት መዳረጉም ነው የሚነገረው።
ስኳሩን ጭነው ከወሰዱት መካከል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው አሽከርካሪ ለኢሳት እንደገለጸው አብዛኛው ምርት በሙቀት ሳቢያ ቀልጦ ለብልሽት ተዳርጓል።
በአሁኑ ጊዜ ከ110ሩ ተሽከርካሪዎች 44ቱ የተበላሸውን ስኳር ጭነው ከሞያሌ ወደ ናዝሬት ተመልሰዋል። በነገው እለትም ወንጂ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሌሎች ተሽከርካሪዎችም በ3 ዙር ከሞያሌ እንደሚመለሱ ነው የተገለጸው።ስኳሩ ወደ ሌላ ሀገር ለመሻገር ያልቻለው ሞያሌ ላይ በኬንያ ድንበር የጉምሩክ ሰራተኞች የቀረጥ ክፍያ ስለተጠየቀበት እንደሆነ ምንጮቻችን ገለጸዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የደረሰበትን ኪሳራ ለማካካስ በዱባይ የሚገኘውን ኩባንያ እከሳለሁ ብሏል።
ስኳሩን ጭኖ ገንዘብ ያልተከፈለው ብራይት ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት ማህበር በበኩሉ ለ2 ወራት ያለስራ የቆምንበትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንን እጠይቃለሁ ነው ያለው።
ለዚህ ሁሉ ኪሳራና ኢትዮጵያውያን በስኳር እጥረት ተቸግረው ወደ ውጭ እንዲሻገር ያደረገው ስኳር ኮርፖሬሽን ተጠያቂ መሆን ቢገባውም ሌሎችን እከሳለሁ ከማለት በስተቀር ስለሱ ጥፋት ያለው ነገር የለም።
ወደ ኬንያ 4 ሺ 400 ቶን ስኳር የላከው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በቅርቡ ከ1 መቶ ሺ በላይ ስኳር ከውጭ ገዝቶ ማስገባቱ ይታወቃል።