(ኢሳት ዜና–መስከረም 29/2010) ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ እንደሚደረግ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ የሚደረገው ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ነው ብለዋል።
መንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደገጠመውም ፕሬዝዳንቱ በይፋ ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ገለጻ በኢትዮጵያ ላለፉት 3 አመታት በነበረው የውጭ ምርቶች መላክ መዳከምና ከዚህ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የወጭ ንግድ ሚዛኑ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል።
በአሁኑ ጊዜም መንግስት ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ስለገጠመው የባቡር ሀዲድ፣የዩኒቨርስቲ ግንባታና ሌሎችም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መሰረተ ልማቶች በዚህ አመት አይካሄዱም ብለዋል።
የታክስ አሰባሰብን በተመለከተም በ2009 ከታቀደው በእጅጉ አንሷል ሲሉ የመንግስት የፋይናንስ እጥረት የሚያሳስብ እንደሆነ ገልጸዋል።
እናም በዚህ አመት በትላልቆቹ የታክስ ከፋዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ የገቢ ማሻሻያ ስርአት እንደሚደረግ ፍንጭ ሰጥተዋል።
በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ የስልጣን መልቀቂያ ያስገቡት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ተገኝተው ስብሰባውን አስጀምረዋል።
የስልጣን መልቀቂያ ማቅረባቸውን በመንግስት ቴሌቪዥን በይፋ ወጥተው ያስታወቁትን አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳን የምክር ቤቱ አባላት ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ አልጠየቋቸውም።
ይህም ያልተደረገው በዛሬው መክፈቻ ሂደት ላይ ጥያቄ ለመጠየቅ ስነስርአቱ ስለማይፈቅድ ሊሆን እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በመክፈቻ ንግግራቸው በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ በማተኮራቸው የስራ አስፈጻሚ ሪፖርት የሚመስል ይዘት እንደነበረው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት መታዘባቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።
ዶክተር ሙላቱ በአመታዊ የመክፈቻ ንግግራቸው የሚያቀርቧቸው ጓዳዮች ሳይፈጸሙ የሚቀሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ እባካችሁ አታስዋሹኝ በሚፈጸሙ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ ጽሁፍ አዘጋጁልኝ በሚል በቅርቡ የውስጥ ማስታወሻ መጻፋቸው አይዘነጋም።
እናም የአሁኑ ንግግራቸው በዚህ አመት በሚወጡ ሕጎች ላይ ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጥ እንዳልነበር ለማወቅ ተችሏል።