(ኢሳት ዜና–መስከረም 25/2010) አለም አቀፉ የሽብር ቡድን አይሲስ ከላስቬጋሱ ነፍሰ ገዳይ ጋር ግንኙነት አለኝ በሚል ያወጣውን መግለጫ ውድቅ የሚያደርጉ ሪፖርቶች በመውጣት ላይ መሆናቸው ታወቀ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የነፍስ ገዳዩ ጓደኛ ለእረፍት ሄዳለች ከተባለበት ከፊሊፒንስ ወደ አሜሪካ ተመልሳ ለአሜሪካ የምርመራ ቡድን አባላት ቃሏን መስጠቷ ታውቋል።
በአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት ላስቬጋስ ከተማ 59 ሰዎችን በመግደል ከ500 በላይ ሰዎችን ያቆሰለው የ64 አመቱ ሴቴፈን ፓዶክ ከወራት በፊት እምነቱን የለወጠ አባሌ ነው በማለት አይ ሲስ መግለጫ ቢሰጥም የፖሊስ መነሻ የምርመራ ውጤቶች እንዳሳዩት ከሆነ ግን ነፍሰ ገዳዩ መሳሪያውን የገዛው ባለፈው አመት መሆኑን አመልክተዋል።
በሆቴሉ ውስጥ ብቻ 23 መሳሪያ የተገኙበት ስቴፈን ፓዶክ ይህን ሁሉ መሳሪያ ሊያከማች የቻለበት ምክንያት እስካሁን ግልጽ አልሆነም።
በላስቬጋስ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 10 ሰአት ከ5 ደቂቃ እስከ 10 ሰአት ከ15 ደቂቃ በዘለቀውና በአጠቃላይ 10 ደቂቃ በፈጀው ተኩስ ወደ 600 ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው የላስቬጋሱ ነፍሰ ገዳይ ጓደኛ ግድያው በተፈጸመ በሁለተኛው ቀን ለእረፍት ሄዳለች ከተባለችበት ፊሊፒንስ ተመልሳ አሜሪካ ገብታለች።
በሎስ አንጀለስ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተመለሰችው ማርሎ ዳንሌይ ለአሜሪካ የምርመራ ቡድንም ስለጉዳዩ ምንም እንደማታውቅ ቃሏን ሰጥታለች።
አሜሪካ ከሚገኘው ከላስቬጋሱ ገዳይ የባንክ አካውንት ፊሊፒንስ ወደሚገኘው ወደርሷ አካውንት የተዛወረው አንድ መቶ ሺ የአሜሪካን ዶላርንም በተመለከተ መኖሪያ ቤት ለመግዛት የላከልኝ ነው ስትል ለመርማሪዎቹ በጠበቃዋ አማካኝነት ተናግራለች።
በመኖሪያ ቤቱና በሆቴሉ ከ40 በላይ የጦር መሳሪያዎች የተገኙበት ስቴፈን ፓዶክ ሆቴሉ ውስጥ ባቆመው መኪና ደግሞ 50 ፓውንድ ተቀጣጣይ ነገሮችና ከ1 ሺ 600 በላይ ጥይቶች መገኘታቸውን ቢቢሲና ሲ ኤን ኤን በዘገባቸው አመልክተዋል።
በሌላ ዜናም ስቴፈን ፓዶክ ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ለማምለጥ እቅድ እንደነበረው የምርመራ ቡድኑ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አመልክቷል።
እንደሪፖርቱ ከሆነም ምናልባትም ፓዶክ ቢያመልጥ ኖሮ አዘጋጅቶ አስቀምጧቸው በነበረው መሳሪያዎች ሌላ ተጨማሪ ጥቃትም ሊፈጽም ይችል ነበር።–ቀጣይ የጥቃቱ ኢላማ የትና እነማን እንደነበሩ ግን የታወቀ ነገር የለም።
ፓዶክ የማምለጥ ሀሳቡን የሰረዘውና ወደ ህዝቡ ሲተኩስ የነበረውን መሳሪያ ወደራሱ ያዞረው በሆቴሉ ውስጥና ውጪ ራሱ ባዘጋጀው ካሜራ አማካኝነት ሰዎች ወደ ክፍሉ መቃረባቸውን በመመልከቱ ነው ሲል ሪፖርቱ ያክላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በርካታ የጦር መሳሪያዎችንና ወደ 1 ሺ ጥይት ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ ትራፊክ መብራት ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በመካከለኛው የአሜሪካ ግዛት ቴንሴ ጆንሰን ሲቲ ረቡዕ ማምሻውን በቁጥጥር ስር የዋለው የ43 አመቱ ስኮት ኤድምሰን አራት ዘመናዊ፣ከፊልና ሙሉ አውቶማቲክ መሳሪያዎችና 900 ጥይቶች ተገኝተውበታል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሲውል ምንም ነገር ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ወዴትና ለምን አላማ እንደሚሄድ ማወቅ አልተቻለም።
ሆኖም ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑ ታውቋል።