(ኢሳት ዜና–መስከረም 25/2010) በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለውና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌደራሊዝም ስርአት አደጋ ላይ መሆኑን የሶማሌ ክልላዊ አስተዳደር አስጠነቀቀ።
የክልሉ አስተዳደር ከሶማሌ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጅጅጋ ምክክር ካደረገ በኋላ የኦሮሚያ አመራሮች ወረራ እየፈጸሙና የግፍ ግድያ እያካሄዱ ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል።
በሶማሌና በኦሮሚያ መካከል የተከሰተው ግጭት በፌደራሉ ጣልቃ ገብነት በርዷል ቢባልም ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው።
የሶማሌ ክልላዊ መንግስትና የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች የኦሮሚያ አመራሮችን ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ሲሉ ወንጅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች ግጭትን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ቢማጸኑም የሶማሊያ አመራሮች ግን የኦሮሚያን ክልላዊ አስተዳደር ክፉኛ ከመወንጀል ወደ ኋላ አላሉም።
የሶማሌ ክልል አመራሮችና የአካባቢው ሽማግሌዎች በጅጅጋ ከተማ ያደረጉትን ምክክር ሲያጠናቅቁ ባወጡት መግለጫ የኦሮሚያ አስተዳደር ወራሪና ጨፍጨፊ ነው ብለዋል።
በሶማሌና ኦሮሚያ መካከል ተፈጥሯል የተባለው ችግር በፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብነት በርዷል ቢባልም ሕወሃት ከበስተጀርባ ችግሩ እንደገና እንዲቀጣጠል ግፊት እያደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።
እንደ ሶማሌ ክልል አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች መግለጫ ከሆነ የኦሮሚያ አመራሮችና ሚሊሻዎች በአካባቢው በፈጸሙት ጥቃት 8 የቱሊ ጉሌድ ወረዳ ነዋሪዎች በግፍ ተገድለዋል።
ሌሎች 18 የሶማሌ ሰዎችም በአሰቃቂ ሁኔታ በኦሮሚያ ታጣቂዎች መገደላቸውን በጅጅጋ የተካሄደው ጉባኤ በመግለጫው አውግዟል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀመድ ጊሌና የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው ኢድሪስ እስማኤል አብዲ የተገኙበት የሀገር ሽማግሌዎች ጉባኤ የኦሮሚያን አመራሮች ወራሪና ተስፋፊ በማለት የፌደራል ስርአቱን በማፍረስ ላይ ናቸው ሲል ኮንኗል።
የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት፣የሶህዴፓ ከፍተኛ አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች ይሕን ሲሉ ታዲያ በኢትዮጵያዊነታቸው እንደማይደራደሩ ግን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የሁለቱን ክልሎች አመራሮች ሰሞኑን ሰብስበው ግጭትን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ተማጽነው ነበር።በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም ወደ ክልሉ በገቡ አጣሪዎች ከተረጋገጠ በኋላ ለፍርድ ይቀርባሉ ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀለውን ሕዝብ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች እንዲያረጋጉና መገናኛ ብዙሃኖቻቸውም ግጭትን ከማራገብ እንዲቆጠቡ ቢጠይቁም ሰሚ አላገኙም።
የሶማሌው ጉባኤ ተሳታፊዎች ግን ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ተገዥ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት።
ይህም ሆኖ ግን የኦሮሚያ መንግስት ከድርጊቱ አልተቆጠበም ሲሉ ኮንነዋል። ለማሳሰቢያው ተገዥ ነን የሚሉት ሶማሌዎችም ኦሮሚያን ከማውገዝ ወደ ኋላ አላሉም።
የሶማሌው ጉባኤ ሲጠቃለል የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የኦሮሚያ አመራሮች ጥቃት እንዲፈጸም እያደረጉ ያሉት ወደብ ለማግኘትና በዚሁም የጦር መሳሪያ ለማስገባት እንዲያመቻቸው ለማድረግ ነው።
እናም አሁን ያለው በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌደራሊዝም ስርአት አደጋ ላይ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አስጠንቅቀዋል።