(ኢሳት ዜና–መስከረም 24/2010)በስፔን የካታላን ግዛት ነዋሪዎች ባለፈው እሁድ መገንጠልን በመደገፍ ድምጽ ከሰጡ በኋላ ውሳኔው አጨቃጫቂ ሆኖ መቀጠሉ ተገለጸ።
የስፔኑ ንጉስ ፊሊፔ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የመገንጠል አጀንዳን ያቀነቀኑት ሰዎች ለሀገሪቱ ሃያልነት ያላቸውን ንቀት አሳይተዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ተገንጣዮቹ የሕግ የበላይነትና የዲሞክራሲ መርህን ጥሰዋል ብለዋል የሀገሪቱ ንጉስ።
ባለፈው እሁድ በስፔን የካታላን ግዛት ነዋሪዎች መገንጠልን በመደገፍ ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል።
90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ መገንጠልን የደገፈበት ይህ ህዝበ ውሳኔ ግን አጨቃጫቂ ሆኖ መቀጠሉ ነው የተገለጸው።
የሀገሪቱ ንጉስ ፊሊፔ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የመገንጠል አጀንዳን ያቀነቀኑት ሰዎች ለሀገሪቱ ሃያልነት ያላቸውን ንቀት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
ተገንጣዮቹ የሕግ የበላይነትና የዲሞክራሲ መርህን ጥሰዋል ሲሉም አክለዋል።
የግዛቲቱ መሪ ካርሰን ፑጂሞንት ግን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ካታላን ነጻነቷን ታውጃለች ብለዋል።
ፑጂሞንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃልምልልስ ማድሪድ ላይ ከተቀመጠው የስፔን መንግስት ጋር በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለ ገልጸዋል።
የስፔን መንግስት ጣልቃ በመግባት ካታላንን ቢቆጣጠርስ ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ ሁሉንም ነገር የሚቀይር ትልቅ ስህተት ይሆናል ብለዋል።
በቋንቋና በታሪክ ከተቀረው ስፔን የተለዩ የሆኑት ካታሎናውያን የመገንጠል ጥያቄ ሲያቀርቡ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም።
በ2014 80 በመቶ ሕዝብ ነጻነትን መርጦ በስፔን ማዕከላዊ መንግስት ተሽሯል።
በራስ ገዝ አስተዳደር ስር ለረጅም አመታት በቆየችው ካታላን በድጋሚ ባለፈው እሁድ በተሰጠው ድምጽ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ከሚሆነው ድምጽ ሰጪ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው መገንጠልን እንደደገፈ ተዘግቧል።
ሆኖም ግን የድምጽ አሰጣጡ በስፔን ፍርድ ቤት እንዲቆም ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ የፖሊስ ሃይል የድምጽ አሰጣጡን ለማስቆም በወሰደው እርምጃ በተፈጠረው ግጭት 900 የሚሆኑ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
33 የሚሆኑ የፖሊስ አባላትም መጎዳታቸውን መረጃዎቹ አመልክተዋል።
በሰሜን ስፔን ከፈረንሳይ ጋር የምትዋሰነው ካታላን የሀገሪቱ ሁለተኛ ከተማን ባርሴሎናን ጨምሮ እጅግ ውብ የሆኑ የውሃ ዳር መስህብ ባለቤትም በመሆኗ በየአመቱ ብዛት ያላቸው ጎብኚዎችን ታስተናግዳለች።
7 ነጥብ 5 ሚሊየን ነዋሪዎች ያሏት ካታላን ጠንከር ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይባትና ሁለት ቋንቋዎች የሚነገርባት ግዛት መሆኗንም ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።
ከአጠቃላይ የስፔን ሕዝብ 16 በመቶ የሚሆነውን የያዘችው ካታላን ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ 19 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ትይዛለች።
በመሆኑም ማድሪድ ያለው ማዕከላዊ መንግስት ለካታላን ከሚሰጠው በላይ ይወስዳል በሚል በካታላን ባሉ ሕዝቦች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።