(ኢሳት ዜና–መስከረም 22/2010) የባህርዳር የምህንድስና ተማሪዎች ዛሬ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ።
በዩኒቨርስቲው ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ምግብ የተከለከሉት ከ1500 በላይ ተማሪዎች ከዛሬ መስከረም 22 ጀምሮ ማንኛውንም የግቢውን ንብረት አስረክበው እንዲወጡ መደረጋቸው ታውቋል።
ተማሪዎቱ በየአብያተ ክርስቲያናት የተጠለሉ ሲሆን የመንግስት ታጣቂዎች ከአንዳንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ተማሪዎቹን እየደበደቡ ሲያስወጡ እንደነበረ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ አራተኛ ዓመት ላይ በሚወስዱት ፈተና ውጤት አሰጣጥ ላይ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ያወጣውን አሰራር በመቃወማቸውና ፈተናውን እንደማይወሰዱ አቋም በመያዛቸው ነው ዩኒቨርሲቲው ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ያደረገው።
ለተማሪዎቹ ድጋፍ እንዲደረግም ተጠይቋል።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ዘርፎች በምህንድስና ትምህርት ክፍል ለአራተኛ ዓመት የደረሱ ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ በመጨረሻም ከግቢው ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የውጤት አሰጣጥ በመቅረቱና በምትኩም መውደቅና ማለፍ ብቻ በሆነው አዲሱ አሰራር ፈተና አንወስደም ያሉት ከ1500 በላይ ተማሪዎች ላለፉት 10ቀናት ያደረጉትን አድማ ተከትሎ ዛሬ ከዩነቨርስቲው እንዲወጡ መደረጋቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ አዲሱን የውጤት አሰራር ለምን ተግባራዊ እንዳደረገ በግልጽ ለተማሪዎቹ አልተነገራቸውም።
ኢሳት የዩንቨርስቲውን አስተዳደር ለማግኘት ያደረገው ሙከራም አልተሳካም። ተማሪዎቹ እንደሚሉት አዲሱ አሰራር ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ በርካታ ተማሪዎችን ለማባረር ሆን ተብሎ የተቀመጠ ነው።
በፊት የነበረው አሰራር ተማሪዎች ውጤታቸው ዝቅ ቢል እንኳን እንዲያሻሽሉ እድል የሚሰጣቸው የነበረ ሲሆን በአዲሱ ግን መውደቅና ማለፍ በመሆኑ የመባረር እድሉ ሰፊ እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ ተማሪዎቹ።
ለቀናት በተቃውሞ የቆዩት ተማሪዎች ከዩንቨርስቲው መልስ ሊሰጣቸው አልቻለም። ካልፈለጋችሁ ግቢውን ለቃችሁ መውጣት ትችላላችሁ የሚለው የዩኒቨርስቲው ማስፈራሪያን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ምግብ እንዳያገኙ ተከልክለዋል።
በአቋማቸው ጸንተው የዩኒቨርስቲውን ውሳኔ ለማስቀየር በተማሪዎቹ በኩል የተደረገው ጫናም ውጤት አላገኘም።
ዛሬ የአንድ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በሙሉ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። የአማራ ክልል ልዩ ሃይል፣ ፈጥኖ ደራሽና መደበኛ ፖሊስ ይህን ለማስፈጸም የዩኒቨርስቲውን ቅጥር ግቢ ወሮታል።
ከ1500 በላይ ተማሪዎች ጓዛቸውን ጠቅልለው ከግቢው ከወጡ በኋላ በባህር ዳር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለጊዜው መጠለላቸውን ነው ያነጋገርናቸው ተማሪዎች የገለጹት።
የመንግስት ታጣቂዎች አንዳንድ ቤተክርስቲያናት ተጠልለው የሚገኙ ተማሪዎችን በዱላ በመደብደብ ሲያስወጡ እንደነበርም የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ትላንት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ላይ ተቃውሞ መሰማቱ ታውቋል።
በእምቦጭ አረም መከላከል ላይ የሚደረገውን ጥረት ለመደግፍ በተካሄደው በዚህ የእግር ኳስ ውድድር ባለፈው ዓመት የተገደሉትን የእሬቻ ሰማዕታት በማስታወስና ለኦሮሞ ወገኖች ድጋፍ በመግለጽ አጋርነት የታየበት እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
ውድድሩ በባህርዳር ስታዲየም እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ተቃውሞ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት ወደባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም መዛወሩን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።