የእሬቻ በዓል ላይ ተሳትፈው ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ የነበሩ አንድ ባስ ሙሉ ታዳሚዎች በፖሊስ ተያዙ

 

(ኢሳት ዜና–መስከረም 22/2010) በተቃውሞ ታጅቦ በተከበረው በዘንድሮው የእሬቻ በዓል ላይ ተሳትፈው ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ የነበሩ አንድ ባስ ሙሉ ታዳሚዎች ትላንት ቃሊቲ ላይ በፖሊስ ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

 

 

በፖሊስ የተያዙትን ሰዎች ለማግኘት የተደረገው ሙከራም አለመሳካቱን ምንጮቹ ገልጸዋል።

 

 

የሕወሃት አገዛዝ ይብቃን ከስልጣንም ይውረድ በሚል ድምጻቸውን ያሰሙት የበአሉ ተካፋዮች የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ፎቶግራፍ በመያዝና ስማቸውን በመጥራት ተቃውሞ ማሰማታቸው ታውቋል።

 

 

ለበዓሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደቢሾፍቱ ደብረዘይት ያመሩት ታዳሚዎች ባለፈው ዓመት የተገደሉትንና በመቶዎች የሚቆጠሩ የእሬቻ በዓል ታዳሚዎችን በህሊና ጸሎት አስበዋቸዋል። 

          

 

ዕሁድ ዕለት ከንጋት ጀምሮ ወደ ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሀይቅ የእሬቻ በዓል ታዳሚ ሶስት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ነበር የተመመው።

 

 

የአባገዳዎች ምክር ቤትና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ውሳኔዎች ተጥሰው የመንግስት ታጣቂዎች በበዓሉ ስፍራ ይገኛሉ የሚለው  የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ በበዓሉ ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ ማድረጉን የሚጠቅሱ ወገኖች የባለፈው ዓመት ዕልቂት እንዳይደገም ስጋታቸውን ገልጸው ነበር። ሆኖም እንደተሰጋው ሳይሆን በዓሉ በሰላም መጠናቀቁ ታውቋል።

 

 

በሁሉም ወገኖች የጥንቃቄ መልዕክቶች የተላለፉበት የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በመንግስት በኩል የተቃውሞ መድረክ እንዳይሆን ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ቢሆንም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም ግን አልተቻለም።

 

 

የእሬቻን በዓል ለማክበር የመጣው ታዳሚ በባለፈው ዓመት የተገደሉትን በማስታወስ በተለይም በስልጣን ላይ ያለው የህወሀት መንግስት አገዛዝ እንዲያበቃ በዘፈን፣ በመፈክርና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተቃውሞ ማሰማቱን ለማወቅ ተችሏል።

 

 

በእስር ላይ የሚገኙትን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮችን / መረራ ጉዲናንና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የሌሎችንም ፎቶግራፎች በመያዝና ስማቸውን በመጥራት በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።

 

 

የዕሁዱ የእሬቻ በዓል ለህወሀት መንግስት ግልጽ መልዕክት የተላለፈበት ነበር።በመንገድ ላይ ሰብሰብ ብለው በዘፈን ጭፈራና መፈክር የሚሰማው የወያኔ አገዛዝ በቃን የሚለው መልዕክት ነው።

 

 

ባለፈው ዓመት የእሬቻ በዓል ላይ የተስተጋባው የወያኔ አገዛዝ ይውደቅ የሚለው መልዕክትም ትላንትም በበዓሉ በስፋት የተስተጋባ መሆኑ በድምጽና በቪዲዮ ከወጡ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል።

 

 

ለበዓሉ ከተለያዩ አከባቢዎች ወደቢሾፍቱ ደብረዘይት የመጡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ትላንት ከቀትር በኋላ ጀምሮ ወደየመጡበት የተመለሱ ሲሆን አንድ አውቶብስ ቃሊቲ ላይ መታገዱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

 

 

በዚህ አውቶብስ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ የበዓሉ ታዳሚዎች በባህላዊ አልባሳት ሆነው ጭፈራ እያሰሙ ሲጓዙ ቃሊቲ ላይ በታጣቂዎች ታግተው ወደፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።

 

 

በርካታ ተመሳሳይ አውቶብሶች አልፈው ይህኛው ለምን እንደታገተ ግን የታወቀ ነገር የለም። የታገቱት ታዳሚዎች ዛሬ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ የኢሳት ምንጮች ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

 

 

በአጠቃላይ የዘንድሮ የእሬቻ በዓል የህወሀት መንግስት ዘመኑ እንዲያበቃ ጠንከር ያለ መልዕክት የተላለፈበት ሆኖ ተጠናቋል።