(ኢሳት ዜና–መስከረም 19/2010)ከአባይ ግድብ ፕሮጀክት ከ2ሺህ በላይ ሰራተኞች መቀነሳቸው ተገለጸ።
በገንዘብ እጥረት ወደፊት መቀጠል ያልቻለው የግድቡ ግንባታ በመጀመሪያው ዙር ከተቀነሱት ሌላ በቀጣይ ሌሎችም እንዲዘጋጁ እንደተነገራቸው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ለበዓል ወጥተው የነበሩ ሰራተኞች በዚያው እንዲቀሩ መድረጉንም ታውቋል።
ከ8ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት የሚነገረው የግድቡ ፕሮጀክት በተከታታይ ዙሮች ሰራተኞቹን እንደሚያሰናብት የውስጥ ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የተለያዩ የፕሮጀክቱ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችም የግድቡን ስፍራ ለቀው መውጣታቸውም ታውቋል።
የቱኒዚያው አብዮት የአረቡን ዓለም ሲያንቀጠቅጥና በአፍሪካውም ቀንድ ትኩሳት ሲፈጥር ድንገት ያለዕቅድ ዱብ ያለው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ሰባት ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ወራት ቀርተውታል።
እንደዕቅዱ ከሆነ ይጠናቀቃል የተባለው በ2008 እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር ነበር። ግንባታው ግን ከ50 በመቶ በላይ መሻገር አቅቶት የዕቅድ ዘመኑ ከተጠናቀቀ ሁለተኛ ዓመቱን ሊጨርስ ነው።
ከህዝብ በተለያዩ መንገዶች በሚሰበሰብ ገንዘብ ይገነባል የተባለው የአባይ ግድብ ከሚያስፈልገው ከ80 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ሩብ ያህሉን እንኳን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ብሄራዊ ስሜትን ለመቀስቀስና የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት በሚል ያለአቅም ተለጥጦ የተጀመረው የአባይ ግድብ እየተንፏቀቀ ሰባት ዓመታትን ከዘለቀ በኋላ አሁን ስንዝር ወደፊት መራመድ አቅቶት ከቆመ ወራት መቆጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የስርዓቱ ባለስልጣናትና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የግድቡን ስራ ተጨማሪ ገንዘብ ለመሰብሰብ የተጋነነ ቁጥር በማቅረብ የጀመሩት የቅስቀሳ ዘመቻ ብዙም ውጤት እንዳላስገኘም ይነገራል።
ህዝብ ከኪሱ ተሟጦ የተወሰደበት ገንዘብ ሳይመለስለት ተጨማሪ የሚሰጠው ባለመኖሩ የስርዓቱ ባለስልጣናት ገንዘብ ፍለጋ ወደውጪ መመልከት መጀመራቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢሳት መረጃ ምንጮች ከስፍራው እንዳስታወቁት የአባይ ግድብ ሰራተኞቹን በገፍ እያባረረ ነው። ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ ከ2ሺህ በላይ የግድቡ ሰራተኞች ተቀንሰዋል። ላለፉት ሰባት ዓመታት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በግድቡ ግንባታ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት እነዚህ ሰራተኞች ድንገት ከስራ መቀነሳቸው የተነገራቸው ሲሆን ለስራ መፈለጊያ የሚሆን ገንዘብ በአካውንታችሁ ይገባል ተብለው በባዶ እጅ እንደተሸኙ ለማወቅ ተችሏል።
እነዚህ የተቀነሱት በመጀመሪያው ዙር መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች በቀጣይ በተከታታይ ዙሮች ተጨማሪ ሰራተኞች እንደሚቀነሱና ይህም ከወዲሁ ለሰራተኞቹ እንዲዘጋጁ እንደተነገራቸው ታውቋል።
የሰራተኞቹ መቀነስ የአባይ ግድብ ግንባታ ከገጠመው የገንዘብ ቀውስ ጋር የተገናኘ መሆኑን የገለጹት ምንጮች ለተከታታይ ወራት ለሰራተኞች ደመወዝ ሳይከፈል መቅረቱን በማስታወስ የግድቡ እጣ ፈንታ አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉም ያክላሉ።
ለግድቡ ስራ የሚውሉ ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ማሽነሪዎች ከአካባቢው መውጣት የጀመሩ ሲሆን ሰሞኑን በርካታ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በቻግኒ አልፈው ኮሶበር የገቡ መሆናቸውን የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከአቅም በላይ ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል የተጀመረው የአባይ ግድብ ስራ የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ይፈታል በሚል የህወሀት ባለስልጣናት ብድር የሚሰጥ ፍለጋ ላይ መጠመዳቸውም ይነገራል።
በሀገር ሀብት፡ በራሳችን እንጨርሰዋለን የሚለው የመንግስት የህዝብ ንቅናቄ መፍጠሪያ ዘመቻ ወደጎን ተደርጎ ገንዘብ ከሚሰጡ የውጭ አበዳሪዎች ጋር የተጀመረው ድርድር እስከአሁን ውጤት እንዳላስገኘም መረጃዎች ያሳያሉ።
ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚንገዳገደው መንግስት በባልስልጣናቱ አማካኝነት ከ75ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ በየዓመቱ ከሀገር ተሰርቆ እንደሚወጣ ይነገራል።
የዓለም ዓቀፍ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት በመሪዎቻቸው አማካኝነት ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ከሚሸሽባቸው ሀገራት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደሟ ናት።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተጋለጠው ደግሞ የአባይ ግድብን በሃላፊነት የሚያሰሩ ከፍተኛ ባልስልጣናትና ባለሙያዎች ሀብት እያሸሹ ሲሆን ሚስቶቻቸው በካናዳና አሜሪካ የፖለቲካ ጥገኘት በመጠየቅ ኑሮ ጀምረዋል። ኢሳት ይህን መረጃ በዝርዝር ለማቅረብ ጥረት የሚያደርግ ይሆናል።