(ኢሳት ዜና–መስከረም 19/2010) እሁድ በሚከበረው የእሬቻ በአል ላይ የመከላከያ፣የፌደራል ፖሊስና የጸጥታ ሃይል እንደሚሰማራ የፌደራል ፖሊስ ገለጸ።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የአባ ገዳዎች ምክር ቤት የታጠቀ የመንግስት ሃይልና ባለስልጣናት በበአሉ ላይ እንደማይገኙ ከገለጸ በኋላ ነው።
በመንግስት ዛሬ የተሰጠው መግለጫ የአባገዳዎቹን ውሳኔ የሚሽርና መንግስት ቀደም ሲል ከሰጠው መግለጫ ጋር የሚጋጭ ነው ተብሏል።
መግለጫው በበአሉ አከባበር ላይ ውጥረት እንዲነግስ ማድረጉንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የፊታችን እሁድ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ የሚከበረውን የእሬቻ በአል በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ አብዩ የጸጥታ ሃይሉን በአካባቢው ለማሰማራት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
ኮሚሽነሩ በዚህ መግለጫቸው ከበአሉ አከባበር ጋር ተያይዞ አመጽ የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን የያዙ ባነሮች፣ጥቁር አልባሳት በመልበስ በአሉን ለማወክ የተዘጋጁ የስለት መሳሪያዎች ፣ጠመንጃ፣ተቀጣጣይ መሳሪያዎች የያዙ፣እንዲሁም መንገድ በመዝጋት የመንግስትና የህዝብ ትራንስፖርት መገልገያ ላይ አደጋ ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ይህ የፖሊስ ኮሚሽነሩ መግለጫ ከኦሮሚያ አባገዳዎች ምክር ቤት ውሳኔ ጋር እንደሚጋጭ ለማወቅ ተችሏል።
የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት በዘንድሮው የእሬቻ በአል ላይ የታጠቀ የመንግስት ሃይልና ባለስልጣናት መንግስትን ወክለው አይገኙም በማለት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በመንግስት የጸጥታ አስከባሪዎች ምትክ 300 በጎፈቃደኛ ወጣቶች ስርአት እንደሚያስከብሩ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰምበቶ መግለጻቸው ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ሃላፊ የሆኑት አቶ ገዛሕኝ አሰፋ ሰርጎ ሊገባ ከሚችል ውጭ የጸጥታ ስጋት የለብንም በማለት ከፖሊስ ኮሚሽነሩ መግለጫ ጋር የሚጋጭ አስተያየት ሰጥተዋል።
የክልሉ የጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ መለሰ ተፈራም መሳሪያ የታጠቀ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል በበአሉ ስፍራ እንደማይገኝ ለቢቢሲ ማረጋገጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።