(ኢሳት ዜና–መስከረም 18/2010)የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፖሊ ቴክኒክ ግቢ የ4ኛና 5ኛ አመት የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ፈተና አንፈተንም በማለታቸው ከተቋሙ መባረራቸው ተነገረ።
በፌደራልና በልዩ ሃይል ተከበው ከግቢ እንዲወጡ የተደረጉት ተማሪዎች ለፈተና ዝግጅት በቂ ጊዜ አልተሰጠንም በማለታቸውና ጥያቄ በማቅረባቸው ተቋሙን ኣእዲለቁ ተገደዋል።
ተማሪዎቹ የመማር ማስተማሩን ተግባር ኢዲሞክራሲያዊና ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ አስተጓጉላችኋልም ተብለዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የፖሊ ቴክኒክ ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ለፈተና በቂ ጊዜ ይሰጠን ባሉ ጸረ ሰላምና ጸረ ጸጥታን የምታውኩ በሚል ህገ መንግስታዊ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው በግቢያቸው ሰሌዳ ላይ በተቋሙ አስተዳደር የወጣው ማስታወቂያ ያሳስባል።
ተማሪዎቹ በ5 ዲፓርትመንት ውስጥ ለአራትና አምስት አመታት በግቢው በመማር ላይ የነበሩና ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ናቸው።
እነርሱም የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፣የምግብ ኢንጂነሪንግ፣የሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ የሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግና የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች መሆናቸውን በማስጠንቀቂያው ላይ የወጣው ማስታወቂያ ያስረዳል።
የኢንጂነሪንግ ፋካሊቲው ባወጣው ማስጠንቀቂያ ፈተና አንፈተንም ያሉ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ሁሉም ግቢዎች ውስጥ በማንኛውም ስፍራ መንቀሳቀስ አይቻልም።
በመኝታ ክፍላቸውም ሆነ በግቢው ውስጥ ቢገኙም ሕገመንግስታዊ ርምጃ ይወሰድባችኋል የሚል ማስጠንቀቂያም ወቶባቸዋል።
ሰላማዊ ጥያቄያቸው በጸረ ሰላም ሃይልነት ያስፈረጃቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በፌደራልና በልዩ ሃይል ተከበው ከግቢ መባረራቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በባህር ዳር የብአዴን ድርጅታዊ ስብሰባ ሲካሄድ በአባላቱ መካከል ልዩነትና ውዝግብ በመፈጠሩ በከተማው ውጥረት መንገሱ ይነገራል።
ተማሪዎች ያነሱት የፈተና ጊዜ ይለወጥልን ጥያቄ በፖለቲካ ተመንዝሮ ሰላምና ጸጥታ በማወክ ያስጠየቃቸውም በባህርዳር ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ግቢ የተባረሩት ተማሪዎች በየአቅጣጫው እየተበታተኑ መሆናቸው ተነግሯል።ባህርዳር አሁንም ውጥረት ውስጥ ትገኛለች።