(ኢሳት ዜና–መስከረም 12/2010)በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሞዎችና በኢትዮጵያ ሶማሌዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ አወገዘ።
የችግሩ ፈጣሪና አስፈጻሚ ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በመሆኑ መፍትሄውም ስርአቱን ማስወገድ ብቻ ነው ሲል የትብብር ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክም ከአዲስ አበባ ድርጊቱን በማውገዝ የስርአቱ ከፋፍለህ ግዛው ውጤት ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ሕወሃት መራሹ ግፈኛ ቡድን ለ26 አመታት የተካነበትን ጎረቤት ከጎረቤት፣ማህበረሰብ ከማህበረሰብ የማናከስና የማጣላት ሴራውን ገፍቶበታል በማለት መግለጫውን የጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ለዘመናት በክፉም በደጉም አብረው የሚኖሩ ማህበረሰቦችን ደም የማቃባቱ ተግባር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል።
ይህ ማህበረሰቦችን በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲተያዩ የሚከናወን ድርጊት የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ለመዝረፍ ጭምር መሆኑንም ገልጿል።
ስልጣን ላይ ያለው የህወሃት ቡድን አንድን ወገን መሳሪያ በማስታጠቅ በሌላው ላይ ፍጅት እንዲፈጽም ማድረጉ በግልጽ የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው ሲል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ገልጾታል።
በምስራቅ ሀረርጌ በኦሮሚያ የአስተዳደር ክልል በሕጻናት፣በአዛውንቶችና በእናቶች ላይ የሚፈጸመው ድርጊት በዘፈቀደ የሚፈጸም ሳይሆን በሕወሃት አመራር በጀትና ሎጅስቲካዊ ድጋፍ የተቀነባበረና የተጠና የዘር ማጥፋት እንደሆነ አመልክቷል።
ከጅምሩ ሕወሃት ለሰላም፣ለአንድነትና አብሮ ለመኖር ያልቆመ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም አሁን የደረሰበት እጅግ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊት በሁሉም ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን አስከትሏል በማለት ሕወሃትን ተጠያቂ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ መግለጫ ከእንግዲህ ይህ ስርአት መንግስት ነኝ ብሎ ይህንን ጨዋ ህዝብ ለአንዲት ቀን እንኳን የማስተዳደር የሞራል ብቃትም ሆነ ሕጋዊነት የለውም በማለት ከተጨማሪ ቀውስ ሀገሪቱን ለመጠበቅ ስርአቱን ማስወገድ የግድ መሆኑን አስገንዝቧል።
በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘመን ኢትዮጵያ ለዘመኑ በማይመጥኑ ኋላ ቀር ሰዎች እጅ መሆኗንም አስገንዝቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክ ከአዲስ አበባ ድርጊቱን በማውገዝ ባወጣው መግለጫ ለዕልቂቱ ፌደራል መንግስቱን ተጠያቂ አድርጓል።
ራሱ ባወጣው ህገመንግስት የማይገዛ መንግስት ለዜጎች በሕይወት መኖርም ሆነ ለሰብአዊ መብት መከበር ግድ አይኖረውም በሚል ርዕስ መድረክ ባወጣው መግለጫ በዋናነት የዕልቂቱ ፈጻሚ የሆነው የሶማሌ ልዩ ሃይል በፌደራል መንግስት እውቅና በሶማሌ ክልል የተቋቋመ መሆኑን አስታውቋል።
የብሔርና የጎሳ ግጭቶች ስምምነት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተካሄደ መሆኑንም በመዘርዘር የችግሩን አሳሳቢነት አመልክቷል።
በግጭቱ ቤተሰባቸውን ላጡ ካሳ፣ለተፈናቀሉ መቋቋሚያ እንዲሰጣቸው ጥሪ ያቀረበው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክ በወንድማማች መካከል ዕልቂት እንዲፈጠር አመራር የሰጡና የፈጸሙ እንዲሁም የተባበሩ ከፌደራል መንግስት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
ሕዝቡም እንደነዚህ አይነት ሰይጣናዊ ድርጊቶችን አንድነቱን በማጠናከር በንቃት እንዲከላከል መድረክ ጥሪ አቅርቧል።