በሰሜን ጎንደር ሊደረግ የታቀደውን ህዝበ ውሳኔ በመቃወም በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 5/2010) በሰሜን ጎንደር በ12 ቀበሌዎች ሊደረግ የታቀደውን ህዝበ ውሳኔ በመቃወም በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ተገለጸ።

ዕሁድ ሊደረግ በታቀደው በዚሁ ህዝበ ውሳኔ ሁለቱም ወገኖች ባለመሳተፍ እቅዱን እንዲያከሽፉም ጥሪ ተደርጓል።

በመተማና ሽንፋ አካባቢዎች ግጭት ተፈጥሯል።

ለዕሁዱ ህዝበ ውሳኔ በህወሀት የተሰማሩ የምርጫ አስፈጻሚዎችም ከየጣቢያ በህዝብ እየተባረሩ መሆኑ ታውቋል።
ከ12ቱ ቀበሌዎች በ4ቱ ምርጫው መራዘሙ የተገለጸ ሲሆን በየአካባቢው ያለው ውጥረት በህዝበ ውሳኔው ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ከሁለት ቀናት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ለቅማንት ለብቻው አስተዳደር ይገባዋል የሚል አቋም ይዞ ቀጠሮ ያስቀመጠለት ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ በሙሉ ሃይሉ ሰሜን ጎንደር ገብቷል።

የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ በዚህ ዙሪያ መግለጫ የሰጡ ሲሆን የአማራና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ህዝበ ውሳኔው በተያዘለት ፕሮግራም መስከረም 7 2010 ከጧቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በእያንዳንዱ ቀበሌ ድምጽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

እሳቸው በ12ቱ ቀበሌዎች ድምጽ መሰጠቱ ይከናወናል ቢሉም በጭልጋ በአራት ቀበሌዎች በተፈጠረ ተቃውሞ ላለተወሰነ ጊዜ ድምጽ መሰጠቱ እንደተራዘመ ተገልጿል።
በህወሀት በኩል ምርጫው የማይቀየር የማይለወጥ እንደሆነ ቢገለጽም የሰሜን ጎንደር ህዝብ ግን አድማ ሊመታ መዘጋጀቱ እየተገለጸ ነው።

የጎንደር ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ለኢሳት በላከው መግለጫ እንደገለጸው እሁድ ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ ሊሰጥ የሚወጣ ሰው የለም።
ለህዝቡ ጥሪ መደረጉንና በዕለቱ ከቤት በመቀመጥ የህወሀትን አጀንዳ ማክሸፍ እንዳለበት አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል።

የድምጽ መስጪያው ዕለት እየተቃረበ ሲመጣ ውጥረቱ የበረታ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰውታል።

በጭልጋ፣ መተማ፣ አለፋ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰ ሲሆን መተማ ፣ ገንድውሃ ፣ ኮኪት ያለው ህዝብ ፡ አስመራጮችን ከቦታው አባሯል፡፡

በመተማ እና በሽንፋ መሀከል በሚገኘው ጉባይ ጀጀህኝ በተባለው አካባቢ ከቅማንትና ከትግራይ ተወላጆች የተወጣጡ 80 የሚሆኑ ዘመናዊ ትጥቅ የታጠቁ ሃይሎች ሰፍረዋል።

በሽንፋ የከባድ መሳሪያ ተኩስ የሚሰማ ሲሆን የስርዓቱ ወታደሮች ለማስፈራራት በየመንደሩ መሳሪያ በተጠመደበት ተሽከርካሪ በመዘዋወር ላይ ናቸው ተብሏል።
በሌሎች ምርጫው ይካሄድባቸዋል በተባሉ አከባቢዎችም ውጥረቱ እያየለ መምጣቱ ታውቋል።

ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በቋራ መስመር ሽንፋ ድረስ ያሉት አካባቢዎች በተኩስ እየተናወጡ ናቸው።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት ወደዚያው መስመር መግባቱ የተገለጸ ሲሆን ከህዝቡ ጋር ተፋጦ እንደሚገኝ ታውቋል።

ምርጫ ሊታዘቡና ሊያስፈጽሙ በህወሀት ስምሪት የተሰጣቸው ግለሰቦች ላይ ህዝቡ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች አስመራጮት እየሸሹ መሆናቸው ታውቋል።

ኮሮጆ በመገልበጥ በህዝበ ውሳኔ ስም የሚፈልገውን ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው የህወሀት መንግስት ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ ባይልም ህዝቡ መስዋዕትነት በመክፈል የህወሀትን ዕቅድ ለማክሸፍ መዘጋጀቱ ተገልጿል።