በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቃዮች ቁጥር ጨመረ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 5/2010) በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው ወደ ድሬዳዋና አዋሳኝ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች መግባታቸው ተገልጿል።

በጂጂጋ የ28 ሰዎች የቀብር ስነስርዓት ዛሬ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፡ ትላንት ምሽት በከተማዋ የተደራጀ ዘረፋ ሲካሄድ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በጂጂጋ ከተማ የሸቀጦችና የምግብ ዋጋ መጨመሩን ከዘጋቢያችን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የሶማሌላንድ መንግስት ጥቃት በመፍራት በካምፕ ውስጥ ለተጠለሉ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ድጋፍ እያደረገ ነው።
ሁለቱም ወገኖች የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀትን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ግንዛቤ ተወስዷል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን መሳሪያ ከማስታጠቅ አንስቶ የተለየ ድጋፍ የሚያደርግለት የህወሀት መንግስት በኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ በኩልም ታጣቂዎችን በማሰማራት ወደ ግጭት እንዲያመሩ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተባብሶ በቀጠለው በሁለቱ ክልሎች መሃል የተጀመረ ግጭት የበርካቶችን ህይወት አጥፍቷል።

እስካሁን ባለው መረጃ ከሁለቱም ወገኖች ከ50 በላይ ሰዎች በባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ መገደላቸው ታውቋል።

በዛሬው ዕለት በሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጂጂጋ የ28ሰዎች የቀብር ስነስርዓት መፈጸሙን መረጃዎች አመልክተዋል።
እነዚህ የተገደሉት ሰዎች በግጭቱ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጸው የሶማሌ ክልል መንግስት ለዚህም ተጠያቂ ያደረገው የኦህዴድን አመራሮች መሆኑን በመግለጫው ጠቅሷል።

ከጂጂጋ ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ እንደሚሉት በዛሬው ዕለት የቀብር ስነስዓታቸው የተፈጸመው ሲቪል ናቸው የሚባለው ከዕውነት የራቀ ነው። በግጭቱ የተገደሉ የሶማሌ ልዩ ሃይል አባላትና ፖሊሶች ናቸው።

ምንም እንኳን ግድያው ለጊዜው የቆመ ቢሆንም የሰዎች መፈናቀል ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።

በዛሬው ዕለትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሶማሌ ክልል ወጥተው በድሬዳዋና አቅራቢያ የኦሮሚያ መንደሮች መግባታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
መፈናቀሉ በሚቀጥሉትም ቀናት የሚጠበቅ ሲሆን በጂጂጋ፣ ውጫሌና በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑትም በጉዞ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል የሶማሌላንድ መንግስት ፡ ጥቃት በመፍራት በካምፕ ውስጥ ለተጠለሉ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የሶማሌላንድ የሀገር ሽማግሌዎችና መንግስት ፣ የሀገራቸውን ወጣቶች በማረጋጋት ላይ ናቸው ተብሏል።

ትላንት ምሽት በጂጂጋ በወጣቶች የተደራጀ የዘረፋ ተግባር የተፈጸመ መሆኑን የዓይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ቦታዎች በምሽት ዘረፋው ሲፈጸምባቸው የክልል ልዩ ሃይል አባላትና የመከላከያ ሰራዊት በስፍራው እንደነበሩም ታውቋል። ዘረፋውን ከማስቆም ይልቅ ሲያበረታቱም ነበር ተብሏል።

በህወሀት መንግስት በስውር ተቀስቅሷል በተባለውና በፊት ለፊት የየክልሎቹ ገዢ ፓርቲዎች የተፋጠጡበት የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ ግጭት ከገባ በኋላ በተለይ በጂጂጋ የኑሮ ውድነት መከሰቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከኦሮሚያ ክልል ወደ ሶማሌ ክልል የሚገቡ ምርቶች ባለፉት ቀናት በመቋረጣቸው በሸቀጦችና የምግብ ዋጋዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ለማወቅ ተችሏል።

ከኦሮሚያ የሚገቡ ምርቶች በተለይም ድንች፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና የመሳሰሉት በሰሞኑ ውጥረት ምክንያት መቆማቸው የተገለጸ ሲሆን በጂጂጋ የሚገኙ የአትክልት መሸጫ ቤቶች መዘጋታቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ቀድሞም በነበረው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የሚሰቃየው የጂጂጋ ነዋሪ ተጨማሪ ችግር እንደመጣበት ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

በሌላ በኩል በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ግጭቱ መቆሙን እየገለጸ ነው። ግጭቱ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመቆጣጠር የመከላከያና የፊዴራል ፖሊስ ከክልሎቹ አመራርና ጸጥታ አካላት ጋር በአካባቢው ተሰማርተዋል ያለው የመንግስት መግለጫ እስከአሁን ስለተገደሉት ዜጎች ምንም ያለው ነገር የለም።