(ኢሳት ዜና–መስከረም 4/2010)የአማራና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንቶች ጠገዴ ወረዳ ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ ልሳነ ግፉአንና የጠለምት አማራ ማንነት ኮሚቴ በጋራ እንደሚቃወሙት አስታወቁ።
ሕወሃትና ተላላኪው ብአዴን በአዲሱ አመት ዋዜማ ለመላው የጎንደር ህዝብ የሰጡት ስጦታ ቢኖር ሰላምና አንድነቱን ሳይሆን አካሉ የሆነውን የጠገዴ ማህበረሰብን ለሁለት እንደ ቅርጫ መቀራመትን ነው በማለት እርምጃውን በጽኑ አውግዘዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የወልቃይትን መሬት ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ እስራት፣ድብደባና ግድያ እንዲሁም ዝርፊያ ሲፈጸምበት መቆየቱን ልሳነ ግፉአን ከጠለምት አማራ ማንነት ጥምረት ጋር ባወጣው የጋራ መግለጫ በዝርዝር አስቀምጧል።
የወልቃይትን ሕዝብ ሙሉ ውክልና ይዘውና የሕዝብ ጥያቄን አንግበው በሰላማዊ መንገድ ፍትህ የጠየቁ የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት በሽብርተኝነት ተወንጅለው በሕወሃት ማሰቃያ ካምፕ መከራ በመቀበል ላይ መሆናቸውንም አስታውቋል።
በሰላማዊ መንገድ ለቀረበው ጥያቄ በተሰጠው የሃይል አጸፋ የተቆጡ የጎንደር ልጆችም መብታቸውን ለማስከበር በመዋደቅ ላይ መሆናቸውን በመግለጫው ያስታወቀው ጥምር ኮሚቴው ጳጉሜ 1/2009 ሕወሃትና ብአዴን የተፈራረሙትንም ውሳኔ እንደማይቀበለው አስታውቋል።
እኛ በመላው አለም የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ዛሬም እንደትላንቱ በአንድነት ከሕዝባችን ጎን በጽናት በመቆም የትግል አጋርነታችንንና አንድነታችንን እንገልጻለን ብለዋል።
ከጳጉሜ 1/2009 ጀምሮ በሕወሃትና በብአዴን መሪዎች አማካኝነት የታወጀው ጠገዴን ለሁለት መክፈል አንቀበልም በማለት በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
የጎንደር አማራ ለምና ታሪካዊ የሆኑትን የግጨውና የጎቤ መንደሮችን ወደ ትግራይ መከለል ፍጹም ሰብአዊነት የጎደለውና አንድን ብሔረሰብ ለሁለት የሚከፍልና የሚለያይ ጭራቃዊ ተግባር በመሆኑ የምንጸየፈውና የምናወግዘው ነው ብሏል መግለጫው።
ልሳነ ግፉአንና የጠለምት የአማራ ማንነት ጥምረት በጋራ ባወጡት በዚህ መግለጫ በኦሮሚያ ክልልና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተካሄደ ያለውን ደም አፋሳሽ ድርጊት በማውገዝ ሕወሃት ኦህዴድና ሶህዴፓን በመጠቀም ወንድማማቾችን እያፋጀ ነው ብሏል።