በኢትዮጵያ በክልሎች መካከል የተፈጠረው የወሰን ችግር የከፋ የሰብአዊ መብት ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ሰብአዊ መብት ጉባኤ አሳሰበ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 4/2010) በኢትዮጵያ በክልሎች መካከል የተፈጠረውና እየቀጠለ ያለው የወሰን ችግር መዳረሻውን ለመተንበይ የሚያስቸግር የከፋ የሰብአዊ መብት ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ሰብአዊ መብት ጉባኤ አሳሰበ።

በአሁኑ ወቅት በአራት ክልሎችና አካባቢዎች ከወሰን ጋር በተያያዘ ችግር መከሰቱና ውጥረት መንገሱን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

 

የሰብአዊ መብት ጉባኤ በክልሎች መካከል ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች በአስቸኳይ እልባት ይሰጣቸው በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ በአራት ክልሎችና አካባቢዎች የወሰን ችግር መከሰቱንና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በዝርዝር አስቀምጧል።

በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው የወሰን ችግር ለመፍታት ቀደም ሲል በሁለቱ ክልሎች የተፈረመው የድንበር ስምምነት ሰነድ እስካሁን እልባት አለማግኘቱን አስታውቋል።

በአንዱ ክልል ውስጥ ይተዳደሩ የነበሩ ቀበሌዎች ወደ ሌላው ክልል መሻገራቸው በሁለቱም ማህበረሰብ ዘንድ የፈጠረው ቅሬታ ለግጭቱ ምክንያት እንደሆነም በሰመጉ መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

በዚህም ከነሀሴ ወር 2009 አጋማሽ ጀምሮ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሜኢሶ ወረዳ እንዲሁም የባሌና ቦረና አዋሳኝ በሆነው በምስራቅ ሀረርጌ ባቢሌና ፊቅ ወረዳዎች በሀዊ ጉደና ወረዳ ግጭት መከሰቱና መቀጠሉን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ መግለጫውን ባዘጋጀበት በ2009 መጨረሻ አካባቢ በጉርሱም ወረዳ፣ቦርደዴና ቦረና ወረዳዎች የግጭት አደጋዎች ማንዣበባቸውንም አስፍሯል።

በኢትዮጵያ ግዛት በክልሎች መካከል የተከሰተው የወሰን ውዝግብና ግጭት በቤንሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልልም መከሰቱ ተመልክቷል።

በዚህም ችግርና ውዝግብ ሰርቦ፣አባያና ደንቢ በሚባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ኦሮሞዎች ከፍተኛ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሰመጉ ገልጿል።

በዚህም በርካታ የኦሮሞ ብሔር አባላት መፈናቀላቸውን ሰመጉ ይፋ አድርጓል።

በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት በሚኖሩባት ገላና፣አባያና የቡሌ ሆራ ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎች በደቡብ ክልል የኮሬ ብሔረሰብ በሚኖርበት በአማሮ ወረዳ ወሰን ለመለየትና ለማካለል በተደረገው እንቅስቃሴ በወንድማማች ህዝቦች መካከል በተከሰተ ተደጋጋሚ ግጭት የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈም ሰመጉ አስታውቋል።

በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ በሚገኙ የሲዳማ ብሔረሰብ አባላትና በወላይታ ዞን በምእራብ አባያ ሁምቦ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የወላይታ ብሔረሰብ አባላት መካከል የተሞከረውን የወሰን ማካለል ሒደት ተከትሎ ከፍተኛ ውጥረት መከተሉንና ይህም ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትል ሰመጉ ስጋቱን ገልጿል።

ከወሰን ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የቀጠለው ሁኔታ በጊዜ ካልተፈታ ስፋቱንና መዳረሻውን ለመተንበይ የሚያስቸግር ሰብአዊ ቀውስ እንደሚያስከትልና ለሐገሪቱም አንድነት አደጋ መሆኑን አሳስቧል።