(ኢሳት ዜና–መስከረም 3/2010)በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ቁጥር በተገኙበት የጀግኖች ምሽት ፕሮግራም ተካሄደ።
በስነስርአቱም ሶስት የጦር ጄኔራሎችን ጨምሮ ለ7 ወታደራዊ ባለሙያዎችና ለቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል የጀግንነት ሽልማት ተበርክቷል።
በጀግኖች ምሽት ክብረ በአል ላይ ተገኝተው ለተመረጡት ጀግኖችና ተወካዮቻቸው ሽልማቱን የሰጡት የኮሪያው ዘማች ሻምበል ማሞ ሀብተወልድ ናቸው።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት በአየር ለአየር ውጊያ የሶማሊያ ጀቶችን መተው የጣሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሸናፊ ገብረጻድቅ በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማታቸውን ሲቀበሉ የሜጀር ጄኔራል መስፍን ገብረቃልን ሽልማት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ተረክበዋል።
በጀግኖች ምሽት ፕሮግራም ላይ ለመገኘትና በአካል ሽልማቱን ለመቀበል ወደ አሜሪካ ተጉዘው የነበሩት ሜጀር ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ በገጠማቸው ድንገተኛ ቤተሰባዊ ጉዳይ ወደ ሀገር ቤት በመመለሳቸው ሽልማቱ በተወካያቸው አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል።
በእለቱ በጀግንነት ስማቸው ከተወደሰው ተሸላሚዎች አንዱ በጦር ሜዳ ሕይወታቸውን ያጡት ኮለኔል ካሳ ገብረማርያም ሲሆኑ ልጃቸው ዶክተር ስንታየሁ ካሳ በስፍራው ተገኝታ ሽልማቱን ተረክባለች።
ዶክተር ስንታየሁ የአባቷን ሕይወት ታሪክና የጦር ሜዳ ውሎ ካሳ ገብረማርያም በሚል ርእስ ለንባብ ማብቃቷም ታውቋል።
የበረራ ባለሙያና የጦር ጀት አብራሪው ኮለኔል ብርሃኑ ውብነህ ለሃገራቸው በጀግንነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከተከለከለ ከፍታ ላይ በፓራሹት በመውረድ ወገኖቻቸውን ለመታደግ ተንቀሳቅሰው የተሰውት የሃምሳ አለቃ ገረመው ሃይለማርያምም በጀግንነታቸው ተመርጠው ለሕልፈታቸው ማስታወሻ ሽልማት በወንድማቸው በአቶ ገነሜ ሃይለማርያም አማካኝነት ተሰጥቷቸዋል።