(ኢሳት ዜና–መስከረም 3/2010) በአማራ ክልል ከሕወሃት ጋር ቅርበት ያላቸው አንዳንድ የቅማንት ተወላጅ ነጋዴዎችና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም የሕወሃት የጦር አዛዦች በጭልጋ አቅራቢያ ሰርባ በተባለ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በሚስጥር መምከራቸው ተሰማ።
በሕወሃት ወታደራዊ አዛዦች የተመራው ስብሰባ የተካሄደው በሰሜን ጎንደር ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድባቸዋል በተባሉ ቀበሌዎች የአማራ ተወላጆችን ነን የሚሉ መብዛታቸው አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ነው።
በሌላ በኩል የሕወሃት ካድሬዎች ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድባቸው 12 የሰሜን ጎንደር ቀበሌዎች በመከላከያ ጸጥታ አስከባሪነት ስም የአካባቢውን ሕብረተሰብ ቅማንት ነኝ እንዲል የግድያ ዛቻና ድብደባ እየፈጸሙ መሆናቸው ምንጮች ገልጸዋል።
በጭልጋ አቅራቢያ ሰርባ በተባለው ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በሚስጥር የተካሄደው ምክክር ከሕወሃት ጋር ቅርበት ያላቸው አንዳንድ የቅማንት ተወላጅ ነጋዴዎችና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም የሕወሃት የጦር አዛዦች የተሳተፉበት መሆኑ ተሰምቷል።
ምክክሩ የተካሄደው ደግሞ በሰሜን ጎንደር ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድባቸዋል በተባሉ ቀበሌዎች የአማራ ተወላጆችን ነን የሚሉ መበራከታቸው አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ነው።
በውይይቱም በሕዝበ ውሳኔው 12ቱን ቀበሌዎች የቅማንት ማድረግ ካልተቻለ በ3 መንገዶች ውጤቱን ለመቀልበስ በሕወሃት በኩል መታቀዱ ምክክር ተደርጎበታል።
በሕዝበ ውሳኔው አማራ ነን የሚሉ ወገኖች ካመዘኑ ደግሞ አንደኛው መንገድ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በመጠቀም ኮሮጆ መገልበጥ ነው።
በአካባቢው ግጭት ማስነሳትና የሕዝበ ውሳኔ ሒደቱን ማደናቀፍ 2ኛው መንገድና ሌላኛው አማራጭ ተደርጎ ተቀምጧል።
በ3ኛ ደረጃ እንደ አማራጭ የተያዘው የምርጫ ውጤቱ ሲገለጽ ውጤቱን አንቀበልም ተጭበርብሯል በማለት ሂደቱ እንዲደገም ማድረግ በሕወሃት የመከላከያ አዛዦች የተመራው ይህው ሚስጥራዊ ስብሰባ ምክክር ያደረገበት አጀንዳ ነው።
ሕወሃት ከፌደራል በተወከሉ የመከላከያ አዛዦቹ አማካኝነት በምርጫው ከወዲሁ ጣልቃ ገብቶ ሂደቱን ማወክ መጀመሩን የኢሳት ምንጮች ከስፍራው ጠቁመዋል።
ይህ ሚስጥራዊ ስብሰባ ከሕወሃት ጋር ቅርበት ባላቸው አንዳንድ የቅማንት ተወላጅ ነጋዴዎች፣የመንግስት ሰራተኞችና በሕወሃት የጦር አመራሮች ሲካሄድ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ደግሞ በባህርዳር የማእከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ናቸው።
የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ሕዝበ ውሳኔው በምርጫ ቦርድ አማካኝነት በፌደራል በኩል የሚካሄድ ነው በሚል ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸውን የቅርብ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
የሕወሃት ካድሬዎች ግን ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድባቸው 12 የሰሜን ጎንደር ቀበሌዎች በመከላከያ የጸጥታ አስከባሪነት ስም የአካባቢውን ሕብረተሰብ ቅማንት ነኝ በሚል ድምጽ እንዲሰጥ የግድያ ዛቻን ጨምሮ በማስፈራራት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።