(ኢሳት ዜና–መስከረም 1/2010) በአሜሪካ የፍሎሪዳ ግዛትን የመታው ኢርማ አውሎ ንፋስ ፍጥነቱን ቀንሶ ወደ ደቡብ ምእራብ አቅጣጫ ማምራቱ ተነገረ።
አውሎ ንፋሱ ከ3 እስከ 4 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎችን ከኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ውጪ አድርጓቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ 75 ማይል ወይም 150 ኪሎ ሜትር በሰአት እየተምዘገዘገ ያለው ኢርማ አውሎ ንፋስ ፍጥነቱን ቀንሶ አቅጣጫውን መቀየሩን በፍሎሪዳ ታምፓ የባህር ዳርቻ ከተማ የሚኖረው ጋዜጠኛ ፋሲል ግርማ ለኢሳት ገልጿል።
በርካታ ኢትዮጵያውያንም አካባቢውን ለቀው ወደ መጠለያ ቦታዎች ገብተዋል ነው ያለው።
ከካሪቢያን ደሴቶች በመነሳት ኩባን ጨምሮ የመታው ዝናብ የቀላቀለው ኢርማ አውሎ ንፋስ እስካሁን የ28 ሰዎችን ሕይወት ማጥፋቱ ታውቋል።
በፍሎሪዳ ደግሞ ከአውሎ ንፋሱ ጋር በተያያዘ 4 ሰዎች መሞታቸውን የቢቢሲና ሲ ኤን ኤን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ከፍሎሪዳ ግዛት 25 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከአካባቢው እንዲወጡም ተደርጓል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢርማ አውሎ ንፋስን አደገኛነት በመግልጽ በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አስታውቀዋል።
ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከልና አካባቢውን መልሶ ለማቋቋም የብሔራዊ ዘብ መሰማራቱም ታውቋል።