(ኢሳት ዜና–መስከረም 1/2010)የኢትዮጵያ አዲስ አመት በኢትዮጵያና በተለያዩ የአለም ክፍሎች በድምቀት ተከበረ።
አዲሱ አመት በልዩ ልዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርአት ደምቆ መዋሉ የታወቀ ሲሆን በተለይ በዋዜማው የሙዚቃ ዝግጅቶች በልዩ ልዩ መድረኮች ለሕዝብ ቀርበዋል።
በቅርቡ አዲሱን የሙዚቃ አልበሙን ለማስመረቅና ከማር እስከ ጧፍ በሚል የተቀነባበረውን ክሊፑን ለመልቀቅ በሒልተን ሆቴል የተጠራው ፕሮግራም በመንግስት የተሰረዘበት ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ለአዲሱ አመት ከማር እስከ ጧፍ የሚለውን የሙዚቃ ክሊፕ ለህዝብ አሰራጭቷል።
የባህል ሙዚቃ ንግስት በመባል የምትታወቀው አንጋፋዋ ድምጻዊ ማሪቱ ለገሰም ለአዲሱ አመት የባህል ሙዚቃ የለቀቀች ሲሆን ከኢሳት ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላትን ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም የአዲሱን አመት መልካም ምኞቷን ገልጻለች።
ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተከበረው የአዲስ አመት ዝግጅት በዝነኛው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያ ዜማ በዋናነት የታጀበ ሲሆን ዘመናዊና ባህላዊ ሙዚቃዎችም ለበአሉ ድምቀት ሰጥተዋል።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ ከአሜሪካ ከተሞች በሲያትል፣አትላንታና ቦስተን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አዲሱን አመት በከፍተኛ ደስታ ተቀብለውታል።
በአውሮፓ ስዊዘርላንድ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ቤይሩትና ዱባይ ብሎም በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አዲሱን የኢትዮጵያውያን አመት በልዩ ድምቀት አክብረውታል።