በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን 118 የሸንኮራ አገዳ ማመላለሻ ተጎታች ጋሪዎችን ለመግዛት የወጣውን ጨረታ በሚስጥር ለሬይስ ኢንጂነሪንግ ለመስጠት መታቀዱ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 30/2009) በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን 118 የሸንኮራ አገዳ ማመላለሻ ተጎታች ጋሪዎችን ለመግዛት የወጣውን ጨረታ በጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ለሚመራው ሬይስ ኢንጂነሪንግ በሚስጥር ለመስጠት ቅድመ ስምምነት መደረጉን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

በሼህ መሐመድ አላሙዲን ከፍተኛ አክሲዮን ድርሻ በባለቤትነት የሚተዳደረው ሬይስ ኢንጂነሪንግ ማሽነሪዎችን ለማስመጣት ከጨረታው በፊት ከአንድ የብራዚል ኩባንያ ጋር መፈራረሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አጋልጠዋል።

የ150 ሚሊየን ብር ግምት ባለው ጨረታ እየተሳተፉ ያሉ የተለያዩ ድርጅቶች የቴክኒካል ሰነዳቸውን ካስገቡ በኋላ በውስጥ መስፈርት ከብራዚል ለተገዙ ማሽነሪዎች ትልቅ ነጥብ እንዲሰጥ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሸንኮራ አገዳ ማመላለሻ ተጎታች ጋሪዎችን ለመግዛት የወጣው ጨረታ በቁጥር ኢፒ/ኦቲ/31/ኤስ ሲ/2016/17 ሰነድ የተመዘገበ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

118 ተጎታች ጋሪዎች 150 ሚሊየን ብር ግምት ዋጋ እንዳላቸውም የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ ጨረታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣና በጉዳዩ ላይ የቴክኒካል ብቃት ያላቸው ኩባንያዎች የተሳተፉበት ነው።

ይህም ሆኖ ግን ጨረታውን በሚስጥራዊ አሰራር በጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ለሚመራውና በሼህ መሀመድ አላሙዲን ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ለሚመራው ሬይስ ኢንጂነሪንግ ለመስጠት ውስጣዊ ሴራ መኖሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል።

እንደ ምንጮቹ ገለጻ ማሽነሪዎቹ ከብራዚል የሚመጡ ከሆነ በጨረታው ከፍተኛ ሰነድ ይሰጣቸዋል።

ይህ መስፈርት ግን ለተወዳዳሪዎች በተሰጠው ሰነድ ላይ ሆን ብሎ እንዲሰፍር አልተደረገም።ይህም በመሆኑ ሬይስ ኢንጂነሪንግ ከጨረታው ከመውጣቱ በፊት ከአንድ የብራዚል ኩባንያ ጋር ተፈራርሞ የሸንኮራ አገዳ ማመላለሻ ተጎታች ጋሪዎችን ለማስመጣት ስምምነት ላይ መድረሱን የመረጃ ምንጮቹ አጋልጠዋል።

በአሁኑ ጊዜ የቴክኒካል ውድድሩ ሆን ተብሎ እንዲዘገይ ከተደረገ በኋላ አለፉ ከተባሉ ኩባንያዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ሬይስ ኢንጂነሪንግ እንደሚገኝበት መረጃዎች አመልክተዋል።

አሁን የቀረው የፋይናንሻል ግምገማ ቢሆንም ጉዳዩ ቀድሞ ያለቀ በመሆኑ ጨረታው ለሬይስ ኢንጂነሪንግ ለመስጠት በውስጥ ለውስጥ የሕወሃቱ ጄኔራል ከስኳር ኮርፖሬሽን ሰዎች ጋር መጨረሳቸውን ምንጮቹ ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ የሙስና ዘመቻ በሚል በሌብነትና በስርቆት የተጠረጠሩ ሰዎች እየታሰሩ ነው ቢባልም አሁንም ዋናዎቹ የሕወሃት ሰዎች የሚነካን የለም በሚል በአቶ አባይ ጸሃዬ እገዛ ዘረፋቸውን መቀጠላቸውን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።