ኢርማ የተባለው አደገኛ አውሎ ንፋስ የአሜሪካ ግዛት ወደ ሆነችው ፍሎሪዳ በመገስገስ ላይ ነው

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 30/2009) ኢርማ የተባለው አደገኛ አውሎ ንፋስ የአሜሪካ ግዛት ወደ ሆነችው ፍሎሪዳ በመገስገስ ላይ መሆኑ ታወቀ።

የፍሎሪዳ ግዛት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን የአሜሪካ የፌደራል መንግስትም ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ኢርማ የተባለው አደገኛ አውሎ ንፋስ ሐርቬይ የተባለው ዝናብ የቀላቀለው አውሎ ንፋስ ሒውስተንን በከፍተኛ ደረጃ ከመታ ከቀናት በኋላ ይከሰታል መባሉ ትልቅ ስጋትን ፈጥሯል።

በቴክሳስ ግዛት ሒውስተን ከደረሰው አደጋ የከፋ ሁኔታ ያስከትላል የተባለው ኢርማ አውሎ ንፋስ አንቲጓንና ቨርጂን የተባሉ ደሴቶችን እየመታ ረቡዕ ከሰአት በኋላ ፖርቶሪኮ ይደርሳል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን አውሎ ንፋሱ በሰአት ከ180 ማይል በላይ እንደሚጓዝም ተመልክቷል።

ይህም በአውሎ ነፋስ መደብ የመጨረሻውን 5ኛውን ደረጃ የያዘ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ በአሜሪካ ግዛት ፍሎሪዳ እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ሆኖም የአውሎ ንፋሱ መምጫም ሆነ መሔጃ አቅጣጫ ለግዜው በውል አለመታወቁንም ከባለሙያዎቹ ትንተና መረዳት ተችሏል።

በዶፍ ዝናብ የታጀበው ሃይለኛው ኢርማ አውሎንፋስ ከ7 እስከ 11 ኢንች የሚደርስ ጎርፍ እንደሚያስከትልም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

የሒውስተንን ቀውስ ተከትሎ እየመጣ ያለው እጅግ ከፍተኛው አውሎ ንፋስ ያሳሰባት ፍሎሪዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

ነዋሪዎቿም ለቀናት የሚበቃ ምግብ እንዲያዘጋጁና ለአደጋ ጊዜ የሚሆኑ አስፈላጊ ነገሮችን እንዲከውኑ ጥሪ ቀርቧል።

ከአርብ ምሽት ጀምሮ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ኢርማ አውሎ ንፋስ የሚያስከትለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመከላከል የፍሎሪዳ ሀገረ ገዢ ለ7 ሺህ ብሔራዊ ዘብ ጥሪ አቅርበዋል።

አርብ ጠዋት ሪፖርት እንዲያደርጉም ተጠይቀዋል።አንድ መቶ የሚሆኑት ከወዲሁ ስራ መጀመራቸው ታውቋል።