በትግራይ ክልል ያለው ልማት በሶማሌ ክልልም ቢተገበር በአካባቢው ለተከሰተው አሳሳቢ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይጠቅማል ተባለ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 30/2009)በትግራይ ክልል ያለው ልማት በሶማሌ ክልልም ቢተገበር በአካባቢው ለተከሰተው አሳሳቢ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይጠቅማል ሲሉ ሶስት ከፍተኛ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት አሳሰቡ።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ሁኔታውን ለመገምገም ወደ ስፍራው የተጓዙት ከፍተኛ ባለስልጣናት በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን ልዩነትም መታዘባቸው ተመልክቷል።

የተለያዩ ጥናቶችና ሪፖርቶች በትግራይ ክልልና በተቀሩት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰፊ ልዩነት እንዳለ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

ባለስልጣናቱ የሶማሌ ክልልን ህዝብ ከገባበት አደጋ እንዲወጣ ለማድረግም ቀጣይነት ያላቸው ተግባራት መከናወን አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት ፋኦ ጄኔራል ዳይሬክተር ጆሴ ግራዚያኖ ዳ ሲልቫና የአለም አቀፉ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዝዳት ጊልበርት ሆንግቦ እንዲሁም የአለም የምግብ ፕሮግራም ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሊ ድርቅ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ከጎበኙ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ የርሃብ አደጋውን ለመሻገር ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በዘላቂነት የሚቋቋሙበትንና አደጋ ሲመጣ በቀላሉ የማይናወጡበት አቅም ሊፈጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

8 ነጥብ 5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረሃብ የተጋለጠበት ይህ አደጋ በተለይ በሶማሌ ክልል እጅግ የጠነከረ ሲሆን ለተከታታይ ሶስት አመታት በአካባቢው ዝናብ አለመጣሉ ደግሞ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው ተመልክቷል።

በርሃብ አደጋው በርካታ የቤት እንስሳትን እያጣ ያለው የክልሉ ህዝብ ድርቁ ከቀጠለ ተጨማሪ እንስሳቶችን እንደሚያጣና ችግሩ እንደሚባባስ ሐጂ አብዲ የተባሉ የማህበረሰቡ መሪ ለከፍተኛ ልኡኩ አሳስበዋል።

ለእኛም ቢሆን በቂ እያገኘን አይደለም ያሉት ሐጂ አብዲ በቂ የምግብ ዕርዳታ ካላገኘን ከፍተኛ ቀውስ ይከተላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በሱማሌ ክልል ያለውንና ከነዋሪው ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ ማለትም 3 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆነው ተጠቂ የሆነበት የርሃብ አደጋ አሳሳቢ በመሆኑ ሶስቱ የተባበሩት መንግስታት ተቋማት ትኩረት መስጠታቸውን ልኡካኑ ገልጸዋል።

ልኡካኑ በአካባቢው ልማትን ማስፋፋት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ልኡካኑ በድርቅ በስቃይ ያለውን የሶማሌ ክልል ጎብኝተው ወደ ትግራይ ከሄዱ በኋላ በትግራይ የታየው ሁኔታ በሶማሌ ክልልም እንዲፈጸም ጥሪ አቅርበዋል።

የተለያዩ ጥናቶችና ሪፖርቶች በትግራይ ክልልና በተቀሩት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰፊ ልዩነት እንዳለ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።