(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 29/2009) የሕወሃት መንግስት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ከፍተኛ አመራር በራሳቸው ፈቃድ እጃቸውን ሰጡ ሲል መግለጫ አወጣ።
የኦብነግ ከፍተኛ አመራር አብዱልከሪም ሼክ ሙሴ በሶማሊያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እንዲሁም በፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትብብር ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ባለፈው ሳምንት የተገለጸ ሲሆን ይህንንም የሚያረጋግጡ የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃዎች መሰራጨታቸው ታውቋል።
የሕወሃት መንግስት ግለሰቡን በፈቃዳቸው እጃቸውን ሰጡ በሚል ለፕሮፓጋንዳ ሊጠቀምበት እንደሚችል ከግንባሩ በተጨማሪ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ቀድመው አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ከፍተኛ አመራር አብዱልከሪም ሼክ ሙሴ ላለፉት ሶስት ኣአመታት በሞቃዲሾ መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ከሞቃዲሾ ለቤተሰብ ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ ተይዘው መታሰራቸውና በኋላም ተላልፈው መሰጠታቸውን ኦብነግ ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ መንግስት አቶ አብዱልከሪም ሼክ ሙሴ በፈቃዳቸው ገቡ ለማለት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ነበር።
እንደተባለውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹና በፓርቲና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አቶ አብዱልከሪም ሼክ ሙሴ ድርጅቱን በፈቃዳቸው በመተው ወደ ሀገር መመለሳቸውን ገልጿል።
ሆኖም የመንግስትን መግለጫ ተከትሎ የኦጋዴን ነጻነት ግንባር በድረገጹና በመገናኛዎች አመራሩ ተገደው መወሰዳቸውን የሚያሳይ የቪዲዮና የፎቶ ምስል አሰራጭቷል።
መንግስት በፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሱ ያላቸው አቶ አብዱልከሪም ሼክ ሙሴ እግራቸው በሰንሰለት ታስረው የሚታዩ ሲሆን በሌላም ሁኔታ በኮማንዶ ፖሊሶች ሲጠበቁም ማየት ተችሏል።