(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 29/2009)የኢትዮጵያ ቀን በሜሪላንድ ግዛት ሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ በድምቀት ተከበረ።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 3 /2017 የተከበረው ይሕ ቀን በርካታ ኢትዮጵያውያን በባህላዊ ምግቦች፣አልባሳትና ታሪካዊ ቅርሶች ደምቀው የታዩበት ነበር።
ኢሳት በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ያናገራቸው ታዳሚዎች ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በአገዛዙና በሌሎች ጠላቶች ዘመቻ በተከፈተበት ሁኔታ በሜሪላንድ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሰጡት የአጸፋ ምላሽ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
በክብረ በአሉ ላይ የተገኙት የሞንጎሞሪ ካውንስል ፕሬዝዳንት ሮጀር በርሊነር ካውንስሉ ለኢትዮጵያውያን ቀን እውቅና የሰጠበትን ሰርተፍኬት ለኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማእከል አስረክበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግርም በአሜሪካ ካሉ አውራጃዎች በቁጥር ብዙ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን በሞንጎሞሪ አውራጃ መኖራቸው ያኮራናል በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።
ያለምንም ጥርጣሬ ኢትዮጵያውያን አውራጃውን በሀብት፣በቢዝነስና በትምህርት እንዲበለጽግ በማድረጋቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያን ይዘውት የመጡት ጠንካራ መንፈስ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነና በአሁኑ ሰአት ደግሞ አሜሪካ እንዲህ አይነት ጠንካራ መንፈስ የምትፈልግበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።