(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 25/2009)በኢትዮጵያ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለውን የምግብ እህል እጥረት በተመለከተ ሶስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ከአርብ ጀምሮ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
ባለስልጣናቱ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ/ዳይሬክተር፣የአለም አቀፍ የግብርና ምርት ፈንድ ተጠሪና የአለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ሃላፊ ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በሐገሪቱ ያለውን አሳሳቢ ድርቅ በተመለከተ ከኢትዮጵያው አገዛዝ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ለማወቅ ተችሏል።
የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት ዩ ኤስ አይዲ ዳይሬክተርም ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ኢትዮጵያ ገብተዋል።
በኢትዮጵያ ተከታታይ የአየር ንብረት መዛባት፣የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ችግርና ሀብትን አብቃቅቶ ያለመጠቀም ችግር በድርቅ ላይ ድርቅን አስከትሏል።
በሀገሪቱ አሁን ያለው ከፍተኛ የምግብ እሕል እጥረት መረር ያለ ርሃብን ማስከተሉም ነው የሚነገረው።
በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ ምግብ የላቸውም፣ለከፋ የምግብ እጥረትም ተዳርገዋል ይላል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጫ።
በተለይ ደግሞ በሐገሪቱ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ለድርቅ አደጋው ተጋላጭ ሆነዋል ተብሏል።
እናም ይህንኑ ጉዳይ ተወያይቶ መፍትሄ ለመስጠት ሶስት የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት የ3 ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ነገ አርብ ኢትዮጵያ ይገባሉ።
እነዚህም ባለስልጣናት የምግብና የእርሻ ድርጅት /ፋኦ/ ዳይሬክተር ጆዜ ግራዚያኖ፣የአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ተጠሪ ግሊበርት ሆውንግቦና የአለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ሃላፊ ዴቪድ ቤይስሉ ናቸው።
ባለስልጣናቱ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችንና ሕጻናትንም የጎበኛሉ ተብሏል።የምግብ እርዳታ አቅርቦቱንም እንዲሁ።
በሶማሌ ክልል ከፍተኛ የከብቶች እልቂት በመድረሱም በአካባቢው ያለውን እንስሳት የመኖ እርዳታ አሰጣጥንም ያያሉ ነው የተባለው።
ይህን ካደረጉ በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን አገዛዝ ባለስልጣናት እንደሚያነጋግሩ ዘገባዎች አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ተቋም ዩ ኤስ አይ ዲ ዋና ዳይሬክተር ማርክ ግሪንም የተከሰተውን የድርቅ ሁኔታ ለማየት በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን አግኝተው በኢትዮጵያ ያለው ድርቅ በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸውላቸዋል።
ይህ የድርቅ አደጋ ባለበትና ከፍተኛ የረሀብ አደጋ ባንዣበበት ሁኔታ የኢትዮጵያን አዲስ አመት ሕዝቡ በፌሽታ እንዲያከብርና የ10 ቀናት ልዩ የበአል ዝግጅት መታወጁ ብዙዎችን አስገርሟል።
ይህም ያለፉትን ስርአቶች ውድቀትና የፌሽታ አከባበር አስታውሷል።
በ1966 የከፋው የወሎ ድርቅና ችጋር በተከሰተበት ወቅት ንጉሱ 80ኛ የልደት በአላቸውን በልዩ ሁኔታ ማክበራቸው፣እንዲሁም ደርግ ሊወድቅ ሲቃረብ የ77ቱ ድርቅ እያለ 10ኛ ልዩ የአብዮት በአሉን ድል ባለ ዝግጅት ማክበሩ የሚዘነጋ አይደለም።
ብዙዎች እንደሚሉት ታዲያ አሁንም ታሪክ እራሱን እየደገመ ይገኛል።