በአሜሪካዋ ቴክሳስ ሀርቬይ አውሎ ንፋስ 30 ሺ ሰዎችን ከቀያቸው ሲያፈናቀል ከ450 ሺ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ እርዳታ እንዲጠብቁ ማድረጉ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 22/2009) በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት የባህር ዳርቻዎች በተቀሰቀሰው ሀርቬይ አውሎ ንፋስ 30 ሺ ሰዎች ከቀያቸው ሲያፈናቀሉ ከ450 ሺ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ እርዳታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታወቀ።

እስካሁንም በቴክሳስና በአካባቢዋ ሀርቬይ አውሎ ንፋስ ስላደረሰው ጉዳት አጠቃላይ መረጃ መስጠት ባይቻልም የግዛቲቱ አስተዳደር ግን በአካባቢው ወደ 400 ሺ የሚጠጉ ዜጎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነዋል።
ከአደጋው ጋር በተያያዘም 2 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል።
ባለፈው አርብ የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት የባህር ዳርቻ ከተማ ናት ከምትባለው ኮርፐስ ክርስቲ የተቀሰቀሰውና በርካቶችን ለከፋ ጉዳት የዳረገው ሀርቬይ አውሎ ንፋስ አሁንም ስጋት መሆኑን የሃገሪቱ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች በመናገር ላይ ናቸው።

ከአርብ ጀምሮ በርካታ የሀገሪቱ ከተሞችን ያዳረሰው ሀርቬይ አውሎ ንፋስ 30 ሺ ሰዎችን መኖሪያ አልባ ሲያደርግ ከ450 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ አሁንም እርዳታ እንዲደረግላቸው በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የአየር ትንበታ ባለሙያዎቹ አሁንም ተጨማሪ ዝናብ እንደሚጥልና የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል በሚል ማስጠንቀቂያ በመጠት ላይ ይገኛሉ።
በኮርፐስ ክርስቲናና በአከባቢዋ 13 ሚሊየን ያህል ሰዎች ከጎርፍ አደጋው ጋር በተያያዘ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ሲ ኤን ኤን በዘገባው አመልክቷል።

20 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በጀልባ ውስጥ ሆነው ቀጣይ የማረፊያ እጣ ፋንታቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የቴክሳስ ግዛት እስካሁን ወደ 20 ኢንች በሚለካ ጎርፍ ተጥለቅልቃለች።

በአብዛኞቹ አካባቢዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

እስካሁንም በቴክሳስና በአካባቢዋ ሀርቬይ አውሎ ንፋስ ስላደረሰው ጉዳት አጠቃላይ መረጃ መስጠት ባይቻልም የግዛቲቱ አስተዳደር ግን በአካባቢው ከ300 ሺ በላይ ዜጎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነዋል።
በሰአት 130 ኪሎ ሜትር ይጓዛል በተባለው ይህ አውሎ ንፋስ የምን ያህል ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ በውል የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም እስካሁን ግን ሁለት ሰዎች ከአደጋው ጋር በተያያዘ መሞታቸው ታውቋል።

በርካታ ህዝብ ይኖርባታል ወደ ተባለችው ሂውስተን ዘልቋል የተባለው አውሎ ንፋስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እርዳታ ጠባቂ ሲያደርግ ከ2 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አማካኝነት እርዳታ ማግኘት ችለዋል።
በየአመቱ 50 ኢንች የሚደርስ ዝናብን ታስተናግዳለች የተባለችሁ ሂውስተን በሁለት ቀናት ብቻ 25 ኢንች የዝናብ ውሃን ማስተናገዷ ነው የተገለጸው።እንደ ሀገሪቱ የአየር ትንበታ ባለሙያዎች አባባል ደግሞ በቀጣዩ ቅዳሜ 25 ኢንች ድረስ የሚለካ ዝናብ ይጥላል ሲሉ ከወዲሁ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ንፋስ ሳይቀላቀ ይጥላል የተባለው ይሄ ዝናብ የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ ይችላል የሚል ስጋታቸውንም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
በሂውስተን 96 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እያገኙ እንደሆነ ቢገለጽም እስካሁን ግን ከ87 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ግን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል።

የየአካባቢዎቹ ባለስልጣናትም ሆኑ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች በተከታታይ እየሰጡ ባሉት አስተያየት በቀጠዮቹ ደቂቃዎች ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮችን መገመት አዳጋች በመሆኑ በማንኛውም ሰአት የሚደረጉ የመከላከል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሀርቬይ የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋስ እንደአውሮፓውያኑ በ2008ና በ2001 ከተቀሰቀሱትና ከባድ ጉዳት ካደረሱት አዎሎ ንፋሶች ጋር ሲነጻጸር የከፋ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።