(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 22/2009) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊውን ኩባንያ በመከልከል ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከሕግ ውጪ የሰጠውን የሕንጻ ግንባታ በተጠናቀቀበት በአሁኑ ወቅት የቢሮ እቃዎቹን የማሟላቱን ስራ ያለ ጨረታ ለአቶ ተክለብርሃን አምባዬ ባለቤት መሰጠቱ ታወቀ።
የኮንስትራክሽን እቃዎቹን እንዲያቀርቡ ተመርጠው የነበሩት በቅርቡ የታሰሩት የአቶ አባይ ጸሀዬ የቅርብ ጊዜ ባለቤት ወይዘሮ ሳሌም ከበደ ነበሩ።
አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ለባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በስጦታ መኖሪያ ቤት መገንባታቸውንም መዘገባችን ይታወሳል።
በሌብነት የተጠረጠሩ ሰዎችን ማሰሩን መንግስት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በተከታታይ ሲገልጽ ቆይቷል።
በተግባር ግን ዋነኞቹን ተዋንያኖች ጨምሮ ብዙዎችን ሳይነካ በቆመበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ የሚፈጸመው ሙስና አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ከአውሮፓ ተገዝቶ መጣ የተባለው ቁሳቁስ ሲገለጥ የቻይና ሆኖ መገኘቱንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዋና ጽሕፈት ቤትነት የሚገነባውን ባለ 46 ፎቅ ግዙፍና ከኢትዮጵያ ረዥም የተባለውን ህንጻ ለቻይናው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በጨረታ የሰጠ ሲሆን ከውሉ ውጪ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ሰብ ኮንትራት ሆነው በመስራት ላይ ናቸው።
በየማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ውስጥ አቶ አባይ ጸሃዬ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይገልጻሉ።
የኮንስትራክሽኝ እቃዎችን እንዲያቀርቡም ተመርጠው የነበሩት በቅርቡ የታሰሩት የአቶ አባይ ጸሀዬ የቅርብ ጊዜ ባለቤት ወይዘሮ ሳሌም ከበደ ነበሩ።
አመታት ከሚወስደውና 266 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከሚፈጀው ባለ 46 ፎቅ ህንጻ ሌላ ባንኩ በልደታ ቤተክርስቲያን አካባቢ የሰራው ህንጻ የተጠናቀቀ ሲሆን ግንባታውን ያከናወነው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽኝ ድርጅት ነው።
ጨረታውን ያሸነፈው ኩባንያ ወደ ጎን ተገፍቶ ተክለብርሃን አምባዬ ግንባታውን ያከናወነበትን ምክንያት የባንኩ ሃላፊዎች ለሰራተኛውም ሆነ ለሚመለከታቸው ወገኖች ማስረዳት አልቻሉም።
የሕንጻው ግንባታ ሲጠናቀቅም የአቶ ተክለብርሃን አምባዬ ባለቤት ለሕንጻው የቢሮና የመታጠቢያ ቤት እቃዎችን እንዲያቀርቡ ያለጨረታ ተሰጥቷቸዋል።
እቃዎቹ ከአውሮፓ እንደሚገቡ የተገለጸ ቢሆንም የእቃዎቹ ዝርዝር ወይንም ኢንቮይስ ከጣሊያን እንደመጡ ተደርገው ቢቀርቡም እቃዎቹ ሲፈታቱና ሲገለጡ ግን የቻይናና የሌሎች የሩቅ ምስራቅ ሀገራት እቃዎች መሆናቸውንም የባንኩ ምንጮች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ያለውንና መጠነ ሰፊ የሆነውን ዘረፋ በተመለከተ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን በተደጋጋሚ አቤቱታ ሲቀርብ መቆየቱን የሚገልጹት የባንኩ ምንጮች አቶ ሰይፉ ቦጋለ የተባሉ የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት ላይ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ክስ መስርቶ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ሆኖም ጉዳዩ እስከነ አቶ አባይ ጸሀዬ ድረስ ስለሚጎተት በአቶ አባይ ጸሀዬ ግፊት ሰውዬው በዋስ እንዲፈቱ ተደርጓል።አሁን ክሱ መቋረጡም ተመልክቷል።
የጸረ ሙስና ኮሚሽን አንዳንድ ሃላፊዎችም አቶ አባይ ጸሃዬ እስካለ በንግድ ባንክ ያሉ ዘራፊዎችን ማቆም አይቻልም ሲሉ መናገራቸውንም የባንኩ ምንጮች ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተንሰራፋውና ሀገሪቱን እያራቆተ ባለው የዘረፋና የሌብነት ተግባር በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አቶ አባይ ጸሀዬ አሁንም ሳይነኩ በስራቸው ላይ መቀጠላቸው ይታወቃል።