(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 18/2009) በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የተጀመረው አድማ በርካታ ከተሞችንና አካባቢዎችን ማዳረሱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ከሕዝቡ ብሶትና በደል ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል የተጠራው አድማ በደቡብና በአማራ የተወሰኑ አካባቢዎችም መከሰቱ ታውቋል።
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ከተካሄደው ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ ቀጥሎ የተካሄደው የኦሮሚያ ክልል አድማ የነጻነት ትግሉ ሀገር አቀፍ መሰረት እየያዘ መምጣቱን እንደሚያመላክት ተንታኞች ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ከትላንት እሮብ ጀምሮ ለ5 ቀናት የተጠራው ከቤት ውስጥ ያለመውጣት የስራ ማቆም አድማ በርካታ ከተሞችንና አካባቢዎችን አዳርሷል።
አድማው በሰበታ፣ቡራዩ፣ሆለታና ለገጣፎ መካሄዱ ተነግሯል።
በመርካቶ ሲኒማ ራስ፣ሸቀጥ ተራ፣ሳህን ተራ፣ ቦምብ ተራና በተለይም ከ7ኛ አስከ ምእራብ ሆቴል የሚቆሙ ተሽከርካሪዎች ስራ ፈተው መዋል ማደራቸው ነው የተገለጸው።
የአምቦ ነዋሪዎች አድማውን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አድርገዋል።ለአንድ አላማ በአንድ ጊዜ የሚካሄድ ትግል እንደሆነ አድማውን የጠሩት የኦሮሚያ ወጣቶች ይናገራሉ።
እናም አድማው በሐረርጌ ፣ባሌ፣ወለጋና አርሲ በስፋት ተግባራዊ መደረጉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በወሊሶ፣ቱሉ ቦሎ፣ፊንጫ፣ወሊሶ፣ቤጊና በመሳሰሉት ከተሞች የንግድ መደብሮች ተዘግተው ተሽከርካሪዎች እንዲቆሙ መደረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም አድማው በደቡብና የአማራ ክልል አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መታየቱን ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።
በደቡብ ክልል ከአርባ ምንጭ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ ሰላም ባስ አውቶቡስ ከጉዞው እንዲስተጓጎል መደረጉ ታውቋል።
በአርባምንጭ ከኦሮሞ ወገኖቻችን ጋር አብረን እንቁም የሚል ወረቀት ተበትኗል።
በአማራ ክልልም ከቡሬ ወለጋ የሚወስደው መንገድ ሲዘጋ የሕዝብ ማመላለሻና የጭነት ተሽከርካሪዎችም ስራ አቁመው መዋላቸው ነው የተነገረው።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አድማው ተግባራዊ በተደረገባቸው አካባቢዎች የመንግስት ታጣቂዎች በየአካባቢው ፈሰው መታየታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱንም ምንጮች ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተካሄደው አድማ ከግብር ጫና ጋር ተያይዞ ተቃውሞ ለማሰማትና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ለመጠየቅ ነው።
ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማው በሕወሃት ኢህአዴግ የሚመራው አገዛዝ በግፍ የጨፈጨፋቸውን ሰዎች ለማሰብና ሰማእታቱን ለመዘከር መሆኑንም በየአጋጣሚው እየገለጹ ይገኛሉ።
ጉዳዩን የሚከታተሉ ተንታኞችና ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው አድማና ሕዝባዊ እምቢተኝነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊመጣ እንደሚችል አመላካች ነው ይላሉ።