(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 16/2009)በኦሮሚያ ከነገ ጀምሮ እስከ እሁድ የሚካሄደው በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች ከወዲሁ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡ ተሰማ።
የአውቶቡስ መናሃሪያዎች የነገውን የስራ ማቆም አድማ በመቱ አውቶብሶች ተጨናንቀዋል።
አድማውን አብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢ ተግባራዊ እንደሚሆንም ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች አመልክተዋል።
በወጣቶች የተጠራውን አድማ በመቀላቀል በርካታ ከተሞች ጥሪውን እየተቀበሉ ነው።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል የተከለሰው የቁቤ መጽሀፍ ተግባራዊ እንዳይደረግ ዛሬ ውሳኔ አስተላልፏል። እርምጃው ነገ የተጠራውን አድማ ለመቀልበስ ነው ተብሏል።
ለ5 ቀናት የሚቆየውና በመላው ኦሮሚያ የተጠራው በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ከወዲሁ እንቅስቃሴው ተጀምሯል። ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚገቡና ከክልሉ የሚወጡ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶብሶች ከዋዜማው ጀምሮ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከአዲስ አበባ በአውቶብስ መናሃሪያዎች በርካታ አውቶብሶች ቆመው የሚታዩ ሲሆን ለተሳፋሪዎችም የሸጡትን ትኬት በመመለስ ላይ መሆናቸውም ታውቋል። በኦሮሞ ወጣቶች የተጠራው አድማን ከኦሮሚያ ባሻገር በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ህዝብም እንዲቀላቀለው እየተጠየቀ ነው።
ወጣቶቹ ይህን የህዝብ ውሳኔ በመጣስ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ከወዲሁ ማስጠንቀቃቸው ተሰምቷል።
በአጠቃላይ ከቤት ውስጥ ያለመውጣትን አድማ መነሻ በማድረግ ወደ ኦሮሚያ የሚገቡና የሚወጡ የትራንስፖርት አገልግሎቶች መስተጓጎላቸው ታውቋል።የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከአማራ ክልል፣ከደቡብ፣ከሶማሌ፣ከቤንሻንጉልና ከኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚወጡና የሚገቡ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ከአድማው ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን በመስጋት አብዛኞቹ ተቋርጠዋል።
በተለይ በአምቦ መስመር የትራንስፖርት አገልግሎቱ 70 በመቶ ከወዲሁ መቋረጡን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ከአሶሳ ወደ ኦሮሚያ የሚገቡ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ቆመዋል።ከነገ ረቡእ ነሐሴ 17/2009 እስከ ነሐሴ 21/2009 ለ5 ቀናት በመላው ኦሮሚያ በሚካሄደው ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ ምክንያት በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ መሆኑ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኦሮሚያ በዩ ኤስ አይ ዲ የገንዘብ ድጋፍ ተሻሽሎ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የቁቤ መጽሀፍ ክለሳ ከእግዲህ ተግባራዊ እንደማይደረግ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በይፋ አስታውቋል።ይህም የነገውን ተቃውሞ ለማስቀረት በኦሮሚያ ርእሰ መስተዳድር የተሰጠ ትእዛዝ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።የቁቤ ክለሳውን ለማካሄድ ዩ ኤስ አይ ዲ 92 ሚሊየን ዶላር እንዳወጣበት ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህ የቁቤ ክለሳ ጥናት በኦሮሚያ ነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ በመግጠሙ ለተቃውሞ ምክንያት እንዳይሆን ተግባራዊ እንደማይደረግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።
ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በበርካታ አከባቢዎች የስርዓቱ ታጣቂዎች በብዛት የተሰማሩ ሲሆን ውጥረቱ ማምሻውን እየበረታ መምጣቱ ታውቋል።
ከሀዋሳ ወደ አዳማ መስመር ከምሽት ጀምሮ የተዘጋ ሲሆን ተሽከርካሪዎች በየአውቶቡስ መናሃሪው ተጨናንቀው እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ይህን አድማ ሌሎችም መቀላቀል እንዳለባቸው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በተለይ ለኢሳት ገለጿል። የግንባሩ የስራ አስፈጻሚ አባል፡ የድርጅት ጉዳይና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር በያን አሶባ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ያለው ትግል የስርዓቱን ተቀባይነት ማጣት ያሳያል። ወደ ሀገራዊና ኢትዮጵያ አቀፍ ትግል መሸጋገር አለበትም ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነገ ስለተጠራው በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በተመለከተ ያለው ነገር የለም። በቅርቡ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የተናገሩት ብዙዎችን እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችሏል። አቶ ለማ ባለፈው በተካሄደው ህዝባዊ ንቅናቄ ወደ ጫካ የገቡ ወጣቶችን በተመለከተ የተናገሩት ‘’እርቧቸው ስልክ ደወሉልኝ። ስልኬን የሰጣቸው ማን እንደሆነ አላውቅም። ድረሱልን ብለው ነው የደወሉት’’ የሚል ነበር። ይህ ንግግራቸው የህዝቡን ቁጣ ያቀጣጥለዋል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ። የነገውን አድማ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮም ‘’ህዝቡ ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ይቀላቀል’’ ሲል ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።