(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 16/2009) በአዲስ አበባ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጤፍ ዋጋ መወደዱ ሕብረተሰቡን በእጅጉ እያማረረ መሆኑ ተገለጸ።
በተለይም የሕዝብ የገቢ አቅም እያሽቆለቆለ ባለበት ሁኔታ የጤፍ ዋጋ መወደዱ የቤተሰብ መናጋት እየፈጠረ መሆኑን በሀገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በተያዘው ክረምት የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ከ3 ሺ ብር በላይ መሆኑ ታውቋል።
መስከረም በየነ በልደታ አካባቢ የምትኖር የአራት ሕጻናት እናት ናት።የቤት እመቤት የሆነችውን መስከረም በየነን ጠቅሶ ፎርቹን ጋዜጣ እንደዘገበው በአዲስ አበባየጤፍ ዋጋ በዚህ መጠን እንደዘንድሮ አሻቅቦ አያውቅም።
ባለፉት 30 አመታት 4 ልጆቿን ስታሳድግ የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 3 ሺህ ብር ደርሶ እንደማያውቅ በምሬት ትናገራለች።
እናም ይህ ዋጋ ከልምድ እንደምትረዳው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታ ስለማታውቅ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ምን ይውጠው ይሆን ስትል ነው የጠየቀችው።
በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ነዋሪዎችን ያነጋገረው ዘጋቢ የጤፍ ዋጋ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር የቻለው በአቅርቦት ማነስ ችግር ነው።
በተለይም ባለፉት 2 እና ሶስት ሳምንታት የጤፍና የሌሎች ጥራጥሬዎች ዋጋ በእጅጉ ጨምሯል ብሏል።የፎርቹን ዘገባ
በመርካቶ ጤፍ የሚያከፋፍለው ታደሰ ከፍያለው የተባለ ነጋዴ 3 አይነት የጤፍ አይነቶችን ለቸርቻሪዎች እያከፋፈለ ይገኛል።
ነጭ፣ሰርገኛና ጥቁር ጤፍ እነዚህን ከ2000 እስከ 2400 ብር እንደሚሸጥና በላተኛው ጋር ሲደርሱም ከ3 ሺ ብር በላይ በሆነ ዋጋ እንደሚሸጡ ገልጿል።
የጤፍም ሆነ የሌሎች ጥራጥሬዎች ዋጋ በእጅጉ መጨመር የጀመረው በኦሮሚያ፣አማራና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ መሆኑንም ይናገራል።
የጤፍ ዋጋ በአዲስ አበባ እየጨመረ የመጣውም ከአድአ፣ደጀን፣አርባምንጭና ከልዩ ልዩ አካባቢዎች ሲመጣ በውድ ዋጋ ስለሚገዛ መሆኑን ነው የገለጸው።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ በእጅጉ ተፈላጊና ተወዳጅ የሆነው የጤፍ ምርት ዋጋ በኢትዮጵያ እየናረ የመጣውም ምርቱ የውጭ ምንዛሪ ለማግኝት ሲባል ወደ ውጭ በብዛት ስለሚላክ መሆኑንም ታዛቢዎች ይናገራሉ።