(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 16/2009) ከሌብነት ጋር በተያያዘ እግድ በተጣለባቸው የኮንስትራክሽን ድርጅቶች የባንክ ተቀማጭ ሒሳብ ውስጥ የተገኘው ገንዘብ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በቢሊየን ብር የኮንስትራክሽን ስራዎችን በሚያንቀሳቅሱት በነዚህ ኩባንያዎች የባንክ አካውንት ውስጥ የተገኘው ከፍተኛው ገንዘብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በታች እንደሆነም ተመልክቷል።
ከ50 የሚበልጡ ዝቅተኛና መካከለኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ነጋዴዎችና ደላሎች መታሰራቸውን ተከትሎ በፍርድ ቤት እግድ የወጣባቸው ከ200 የሚበልጡ ግለሰቦች ናቸው።
አራት የኮንስትራክሽን ድርጅቶችም ንብረታቸው በአጠቃላይ ሀብታቸው እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ እንዲሁም ለሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ መታገዱ ይታወሳል።
እግድ ከተጣለባቸው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ከፍተኛ ገንዘብ በባንክ ተቀማጩ የተገኘው ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን ይህም 350 ሺህ ብር እንደሆነ ተመልክቷል።
የበርካታ መቶ ሚሊየን ብሮችና የቢሊየን ብሮች ፕሮጀክቶችን በሚያንቀሳቅሱት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች የባንክ ተቀማጭ ሒሳብ ውስጥ የተገኘው ከፍተኛው ገንዘብ 350 ሺ ብር ሲሆን ሌሎቹ አሰር ኮንስትራክሽን 105 ሺ እንዲሁም የማነ ግርማይና ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን በባንክ ተቀማጫቸው የተገኘው ከ150 ሺ ብር በታች እንደሆነም ምንጮች ገልጸዋል።
የኮንስትራክሽን ድርጅቶቹ ፕሮጀክቶቹን እያካሄዱ ባሉበት ወቅት በባንካቸው የተገኘው ገንዘብ ከመቶ ሺ እስከ 350 ሺ ብቻ መሆኑ በአንድ በኩል መረጃ ስለደረሳቸው ቀድመው ገንዘቡን እንዳሸሹ ሲገመት በሌላም በኩል በባንክ ብድር ስራቸውን እየሰሩ ትርፋቸውን ከሀገር እያሸሹ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።
ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ከኦህዴድ አመራሮች ጋር ቅርበትና ሽርክና እንዳለው የሚጠቀስ ሲሆን አሰር ኮንስትራክሽን የዶክተር አርከበ እቁባይና የቤተሰባቸው ከፍተኛ ድርሻ ያለበት የኮንስትራክሽን ድርጅት መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይገልጻሉ።
የማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ በአቶ አባይ ጸሃዬ ድጋፍ የተቋቋመና የርሳቸውም ከፍተኛ ድርሻ ያለበት የኮንስትራክሽን ድርጅት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።
ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን ድርጅት ንብረትነቱ በአቶ ዳንኤል ማሞ የተመዘገበና የሚንቀሳቀስ ሲሆን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከዚህ ድርጅት ጋር ከፍተኛ የጥቅም ቁርኝት መፍጠራቸውም ተመልክቷል።
የሌብነት ዘመቻውን እየመራ ያለው የሕወሃት ቡድን ከፍተኞቹን ባለስልጣናት ሳይነካ ስርስሩን የጀመረውን ዘመቻ በመቀጠል ተጨማሪ ነጋዴዎችንና የስራ ሃላፊዎችን ለማሰር በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል።
በሕዝብ ዘንድ የሌብነት ምልክት ተደርገው እየታዩ ያሉትን አባይ ጸሐዬን ሳይነካ የቀጠለውን ሌቦቹን የማሰር ርምጃ በታዛቢዎች ዘንድ ለታይታና የውስጥ ቅራኔን መምቻ ተደርጎ እየተጠቀሰ ይገኛል።