(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 15/2009)በአሜሪካ ታላቅ የተባለ የጸሐይ ግርዶሽ ተከሰተ።
ጸሐይ ሙሉ በሙሉ በጨረቃ የተሸፈነችበት ግርዶሽ በተለይ በአሜሪካ ምእራብ ዳርቻ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመመልከት ታድለዋል።
በአሜሪካ ኦሪጎን፣በደቡብ ካራሎይና ቻርልስተን የጸሀይ ግርዶሹን ሙሉ በሙሉ ለመመልከት ብቻ በሚሊየን የሚቆጠሩ ጉብኚዎች መገኘታቸውን የአለም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሜሪላንድ በሚገኘው የሕዋ አየር ሁኔታ ምርምር ጣቢያ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጥላዬ ታደሰ እንደገለጹት ጨረቃ በምድርና ጸሃይ መካከል ሙሉ በሙሉ ትይዩ ስትሆን ግርዶሹ ይከሰታል።
ይህም ለምርምራችን ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ይህ ክስተት በ99 አመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚከሰት በመሆኑ አሁን ያለው ትውልድ እንደገና ይህን የጸሐይ ግርዶሽ ሙሉ ለሙሉ የሚያይበት እድሉ እጅግ ጠባብ ነው።
እናም በጸሀይ ጨረር አይን እንዳይጎዳና ለአይነስውርነት ሊዳርግ ስለሚችል ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው መነጽር ግርዶሹን አሜሪካውያን በአደባባይ ሲመለከቱ ውለዋል።
በጸሀይ ግርዶሹ ሳቢያ ጁፒተር፣ቬነስ፣ሜርኩሪና የመሳሰሉት ፕላኔቶች ከወትሮው ለየት ብለው በማንጸባረቅ ሲታዩ እንደነበርም ዘገባዎች አመልክተዋል።
በጸሀይ ግርዶሹ ሳቢያ የተወሰኑ የአሜሪካ አካባቢዎች ወደሙሉና ከፊል ጨለማነት ተቀይረው እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ተመልክተዋል።