የጋምቤላ ክልል ለብሔረሰቦች በዓል የተበደረውን 346ሚሊየን ብር ከዓመታዊ በጀቱ እየከፈለ መሆኑ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 15/2009)የጋምቤላ ክልል ባለፈው ዓመት ለተከበረው የብሔረሰቦች በዓል የተበደረውን 346ሚሊየን ብር ከዓመታዊ በጀቱ እየቀነሰ መክፈል መጀመሩ ታወቀ።

የመንግስት ልሳን አዲስ ዘመን ጋዜጣ የጋምቤላ ክልል ባለስልጣንን አነጋግሮ እንደዘገበው ለ10ኛው የብሄረሰቦች በዓል ከፌደራል መንግስት የተበደረውን ብር በየዓመቱ ከሚሰጠው በጀት እየቀነሰ ተመላሽ ማድረግ ጀምሯል።
የዘንድሮው የብሔረሰቦች ቀን በአፋር ክልል ሰመራ የሚከበር ሲሆን ለበዓሉ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች 1.6 ቢሊየን ብር መመደቡ ተገልጿል። ብሩ ከህዝብ የሚሰበሰብ ነው ተብሏል።

የጋምቤላ ክልል ከተበደረው 346 ሚሊየን ብር እያለቀ ባለው 2009 200ሚሊየን ብር የከፈለ ሲሆን ቀሪውን 146 ሚሊየን ብር ደግሞ ከመጪው ዓመት በጀቱ ላይ በመቀነስ ለፌደራል መንግስት እንደሚከፍል አስታውቋል።
የጋምቤላ ክልል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ ላክዴር ላክባክ ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲገልጹ ከክልሉ በጀት ላይ ተቀንሶ የሚከፈለውና ለብሄረሰቦች በዓል ወጪ የተደረገው ገንዘብ በክልሉ ላይ ጫና መፍጠሩን አልደበቁም።

በፌደራል መንግስት በጀት በድጎማ የሚንቀሳቀሰው የጋምቤላ ክልል ለአንድ ቀን ድግስ የበጀቱን 1/6ኛውን ወጪ ማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
ሃላፊው አቶ ላክዴር በብድር ለተደገሰው የብሄረሰቦች በዓል የእንግዳ ማረፊያ ህንጻዎችን፣ ስታዲየም፣የመሰብሰቢያ አዳራሾችንና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግንባታዎችን ለማከናወን መዋላቸውን ጠቅሰዋል።
እንደነዚህ ዓይነት ግንባታዎች ሲካሄዱ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ያለጨረታ የግንባታውን ስራ የሚያከናውኑት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አባል የሆኑ የተቋራጭና የኮንስትራክሽን ድርጅት ያላቸው እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለ2010 የጋምቤላ ክልል 2 ነጥብ 3 ቢለየን ብር በጀት የተፈቀደለት ሲሆን ከዚህም ለብሄረሰቦች በዓል የተበደረውን 146ሚሊየን ቀሪ ገንዘብ እንደሚከፍል ሃላፊው አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ክልል ከተመደበለት በጀት እየቀነሰ መልሶ ለፌደራል መንግስት ገቢ ያደርጋል የሚለው ሀሳብ ከአሰራር አንጻር ግራ የሚያጋባ እንደሆነ የገለጹ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጋምቤላ ክልል ባለስልጣን የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የኮንስትራክሽን ድርጅቶችን ለመጥቀም ካልሆነ በቀር ክልሉ ያተረፈው ነገር የለም ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል በራሱ የሚያመነጨው ገቢ የሌለው፡ በክልሉ የሚኖረው ህዝብ በተለያዩ ስር የሰደዱ ችግሮች የሚሰቃይ መሆኑን የሚገልጹት እኚህ ባለስልጣን፡ በጋምቤላ ክልል ስም ገንዘቡን የሚወስዱት የህወሃት አባል የሆኑ ባለሀብቶች ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ የ2010 የብሄረሰቦች በዓልን ለማክበር የተመረጠው የአፋር ክልል 1ነጥብ6 ቢሊየን ብር መመደቡ ታውቋል። የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ለኢሳት እንደገለጸው ለአንድ ቀን በዓል የተመደበውን 1ነጥብ6 ቢሊየን ብር እንዲከፍል የተወሰነበት የአፋር ክልል ህዝብ ነው።

የመንግስት ሰራተኞች፣ ነጋዴዎችና ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የሚከፍሉት የገንዘብ ተመን በክልሉ መንግስት ተወስኖባቸው እንዲከፍሉ በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።
በምግብ ለስራ የታቀፉና የዕርዳታ እህል እየተሰፈረላቸው የሚኖሩ ተረጂዎች ሳይቀር ለብሄረሰቦች በዓል ገንዘብ እንዲያዋጡ መገደዳቸውን ነዋሪዎች በምሬት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ድምጽ
የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት እንዳስታወቀው፡ ለአንድ ቀን ጭፈራ የተመደበውን በቢሊየን የሚቆጠር ብር እንዲከፍል የተፈረደበት የአፋር ክልል ህዝብ በድርቅና ረሃብ እየተሰቃየ ነው።

የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ባለሀብቶችን ለመጥቀም ተብሎ የስታዲየም፣ የአዳራሽና ሆቴል እንዲሁም የአውሮፕላን መንደርደሪያ ግንባታ የተዘጋጀ ገንዘብ ነው ያሉት የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ ለበአሉ በሚል የሚሰሩትና የሚስፋፉት ግንባታዎች በሙሉ ለትግራይ ተወላጅ ለሆኑ ተቋራጮችና የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤቶች ተሰጥተዋል።

ድምጽ
የብሄርሰቦች በዓል መከበር የጀመረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት በምርጫ 97 ከፍተኛ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከሽንፈት ድንጋጤ ለመውጣት በሚል ከተጀመሩት በዓላት አንዱ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተመድቦ በጭፈራና ዳንስ ለአንድ ቀን የሚከበር ነው።

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፉት 10ዓመታት ለዚህ በዓል የሚመደበውን በርካታ ሚሊዮን ገንዘብ የሚከፋፈሉት ከስርዓቱ ጋር የጥቅም ግንኙነት ያላቸው ባለሀብቶች ናቸው። የዘንድሮው የአፋሩ በዓል 1ነጥብ6 ቢሊየን ብር የተመደበለት መሆኑም አነጋጋሪ ሆኗል።