(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 15/2009)በኢትዮጵያ የታቀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውጤታማ አለመሆናቸውን በአቶ አባይ ጸሃዬ የሚመራው ተቋም ያጠናው ጥናት አመለከተ።
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል የተካሄደው ጥናት በስኳር፣በቤቶች ግንባታ፣በመንገድና ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች የታቀዱ ስራዎች መውደቃቸውንና ከፍተኛ የህዝብ ንብረቶች ዝርፊያና ውድመት ማስከተላቸውን በኢሳት እጅ የገባውና በባለ 327 ገጹ ሪፖርት አመልክቷል።
ከነዚህ ካልተሳኩ ፕሮጀክቶች ጋርም ተያይዞ 77 ቢሊየን ብር አላግባብ መባከኑን ጥናቱ አመልክቷል።
የመንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሀሳቦች በሚል ርእስ የተጠናውና በኢሳት እጅ የገባው ባለ 327 ገጽ ሰነድ ይሰራሉ ተብለው የታቀዱት ትላልቅ ፕሮጀክቶች አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ያለምንም ውጤት የህዝብ ሀብትና ንብረት በከንቱ የባከነባቸው መሆኑን አመልክቷል።
ከመሬት ማፈናቀልና በቂ ካሳ ካለመክፈል ጀምሮ ህብረተሰቡን የሚጎዱ በርካታ ድርጊቶች ተፈጽመዋል።
የፕሮጀክቶቹ የአመራር ስርአትም በአካባቢ ልጅነት፣በትውውቅና በጥቅም ትስስር የሚመራ በመሆኑ በሙያተኛና ሰራተኛ መካከል ቡድንተኝነትና አድርባይነት እንዲፈጠር አድርጓል።
ሙያተኞችና ሰራተኞች ችግሮችን በተጋሩ ቁጥር በሚደርስባቸው ማስፈራራትና ዛቻ እንዲሸማቀቁና ስራቸውን ጥለው እንዲሄዱ ሆኗል።
በተለይም በአቶ አባይ ጸሃዬ ዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመራ የነበረው የስኳር ፕሮጀክት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ2003 እስከ 2007 ባለው ጊዜ እፈጽማቸዋለሁ ካላቸው እቅዶች 73 በመቶውን መፈጸም አልቻለም።
የ27 በመቶ አፈጻጸም የታየውም ቀድሞ በነበሩ የስኳር ፋብሪካዎች ማስፋፊያ እቅድ እንጂ አዲሶቹ አስር ፕሮጀክቶች አንዳቸውም አልተሳኩም።በነዚህ ባልተሳኩ ፕሮጀክቶችም ሰበብ 77 ቢሊየን ብር አላግባብ መባከኑን ጥናቱ አመልክቷል።
ለዚህ ዝቅተኛ አፈጻጸም ዋናው ምክንያት በመጀመሪያው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዘመን በእቅዱ ከተያዙት 10 የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱም እንኳን ወደ ስራ ሊገባ ባለመቻሉ ነው ሲል ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
በህወሃቱ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራውና ብዙዎቹን የስኳር ፕሮጀክቶች ኮንትራት በመውሰድ የሚሰራው የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/የተቋሙን አመራሮችና ሰራተኞች በማሸማቀቅ ስራ ለቀው እንዲሸሹ ማድረጉን ጥናቱ አመላክቷል።
የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ችግሮችን ሲያነሱ ከሜቴክ የሚሰጣቸው ምላሽ የአመለካከት ችግር አለባችሁ የሚል የሚያሸማቅቅና ጥያቄዎችን ደግመው እንዳይነሱ የሚያፍን አካሄድ የተስተዋለበት እንደሆነም በሪፖርቱ በዝርዝር ተመልክቷል።
ለስኳር ፕሮጀክቶቹ ውድቀት ዋነኛ ምክንያት ኮርፖሬሽኑን በተደጋጋሚ የመሩት ሃላፊዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንጂ የዘርፍ እውቀት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ በፕሮጀክት አመራር እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ለማሳተፍ ፍቃደኝነት አለመኖሩ ደግሞ ሌላው ችግር ተደርጎ በጥናቱ ላይ ተቀምጧል።
ይህ አይነቱ የኮርፖሬሽኑ አስተሳሰብና አመለካከት በአሁኑ ሰአት በሁሉም የተቋሙ አመራሮች የተላለፈ ወረርሽኝ ሆኖ ድርጅቱን የባሰ አዘቅት ውስጥ እንደከተተው የጥናቱ ማጠቃለያ አመላክቷል።