(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 12/2009)በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ድንበር ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት መባባሱ ተገለጸ።
በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሃት የተለየ ድጋፍ የሚደረግለት የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል አወዛጋቢ በተባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ግድያ፣ ድብደባና አስገድዶ መድፈር እየፈጸመ መሆኑንም ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ኦብነግ ለኢሳት እንዳስታወቀው የህወሃት መንግስት በሶማሌ ልዩ ሃይልና በስውር ባስታጠቃቸው የኦህዴድ ሚሊሺያዎች አማካኝነት የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ ነው ብሏል።
ከዚህ ግጭት ጀርባ የህወሃት እጅ እንዳለበት የጠቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ኦብነግ ህወሃት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ግጭቱ መቀጠሉ አይቀርም ብሏል።
ኦብነግ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉንና በህወሃት ሰራዊት ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሱ ውጊያዎች መካሄዳቸውንም በመግለጪያው ጠቅሷል።
የይገባኛል ጥያቄ የተነሳባቸውና ውዝግብ ያልተለያቸው 400 የሚሆኑና በሁለቱ ክልል ድንበር ላይ የሚገኙ ቀበሌዎች ላለፉት ስድስት ዓመታት ግጭት አልተለያቸውም።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2005 የተደረገው ህዝበ ውሳኔ ግጭት እንዳይፈጠር ከማድረግ ይልቅ እንዲባባስ አድርጎታል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
ይህም ጉዳዩ የይገባኛል ጥያቄ ሳይሆን ከጀርባው የሁለቱን ህዝቦች ዕልቂት ለፖለቲካ ጥቅም ለማዋል ታቅድ የተጎነጎነ ሴራ ነው ለሚሉ ወገኖች ማስረገጫ ሆኗል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ በሁለቱ ህዝቦች ደም የፖለቲካ ትርፍ ያሰላው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ለሁለቱም ወገኖች ካራ በማቀበል እርስ በእርስ እንዲጋጩ እያደረገ ነው ሲል ለኢሳት ገልጿል።
የግንባሩ ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ሀሰን አብዱላሂ እንደሚሉት ለዘመናት ያለግጭት አብረው የኖሩ የሶማሌና የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ባለፉት 10 አመታት ውስጥ ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት የገቡበት ምክንያት ግልጽ ነው።
የህወሃት መንግስት በህዝቦች መተላለቅ የተገነባ የስልጣን ወንበር ላይ የተቀመጠ ስርዓት በመሆኑ እንደነዚህ ዓይነት ግጭቶች የተለመዱ ናቸው ይላሉ አቶ ሀሰን አብዱላሂ። ከዚህ ግጭት ጀርባ የህወሃት ፍላጎት አለበትም ይላሉ።
በሁለቱ ክልሎች ድንበር ላይ ባሉ አወዛጋቢ ቀበሌዎች እየተካሄደ ባለው ግጭት በርካታ ዜጎች እየሞቱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሰሞኑ ግጭቱ ተባብሶ፡ የሟቾች ቁጥርም በመጨመር ላይ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፡ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ቀያቸውን ለቀው በመሰደድ ላይ ናቸው።
መንግስት ግጭቱን ለማስወገድ የሁለቱ ክልሎችን መሪዎች በፊርማ አስማምቼአለሁ ካለ ወራት ያለፉ ቢሆንም ችግሩ እየከፋ ከመምጣት ሊያቆመው እንዳልቻለ ይነገራል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ እንደሚለው ለዚህ ዕልቂት በዋነኝነት የሚጠየቁት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ናቸው። በተለይ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል የሚፈጽመው ግድያና ኢሰብዓዊ ድርጊት አስከፊ በመሆኑ ከተጠያቂነት አያመልጥም ይላሉ አቶ ሀሰን።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግን ጨምሮ እንዳለው የይገባኛል ጥያቄ ካለም መፈታት ያለበት በፍትሃዊ አሰራር እንጂ በህዝቦች የደም ግብር ሊሆን አይገባም።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በህዝቦች መሃል የሚፈጠሩ ግጭቶች በሙሉ በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት እጁን ያስገባባቸው፡ መፍትሄ እንዳያገኙም ሆን ብሎ በማባባስ ስለሆነ ስርዓቱ ካልተወገደ በቀር ወደፊትም በኢትዮጵያውያን መሀል የእርስ በእርስ ግጭቱ መቀጠሉ የማይቀር ነው ብለዋል – የግንባሩ ከፍተኛ አመራር አቶ ሀሰን አብዱላሂ።
በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል ህዝብ በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ድርቅና ረሃብ እየተሰቃየ ነው ያለው። የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ በህወሀት መንግስትም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየቀረበ ያለው መረጃ በክልሉ የተጋረጠውን አደጋ የማያሳይ ነው ብሏል። የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት 3.2 ሚሊየን የሚጠጋው የሶማሌ ክልል ህዝብ ለረሃብና ድርቅ ተጋልጧል። የኦብነግ ከፍተኛ አመራር አቶ ሀሰን አብዱላሂ ግን ይሄ አሀዝ ትክክል አይደለም። በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል በረሃብና በድርቅ ያልተጠቃው ጥቂት ነው። 5ሚሊየን የሚሆነው የክልሉ ህዝብ አደጋ ውስጥ ገብቷል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ሰሞኑን ወታደራዊ ድል እንደተቀዳጀም አስታውቋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ሶስት አካባቢዎች ከስርዓቱ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ መግጠሙን የገለጸው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ በመንግስት ሰራዊት ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ ነው ብሏል።
በጅጅጋ፡ በአዋሬ ወረዳና በደቡብ ኢሜ አካባቢዎች ውጊያ መደረጋቸውን የገለጸው ግንባሩ በርካታ የመንግስት ታጣቂዎችን ሙትና ቁስለኛ አድርጌአለሁ ብሏል።
ግንባሩ አደረስኩት ስላለው ጉዳትም ሆነ ተደረገ ስለተባለው ውጊያ ከመንግስት በኩል ማረጋገጪያም ሆነ ማስተባበያ አልተሰጠም። ኢሳት ከሌላ ወገን ለማጣራት ያደረገው ሙከራም አልተሳካም።