(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 12/2009) ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳና የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ትእዛዝ ሰጠ።
የሕወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናቱ ከጥቅምት 27-ጥቅምት 29/2010 ባለው ጊዜ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የታዘዙት ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/አመራሮች ከእነ አቶ በቀለ ገርባ ጋር በተያያዘ የመከላከያ ምስክሮች እንዲሆኑ በመጠራታቸው ነው።
በእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ለአራት ተከታታይ ቀናት የመከላከያ ምስክሮችን ሲሰማ የቆየው ፍርድ ቤቱ በዛሬ ውሎው አቃቢ ሕግ እርቦኛል ምሳ ልብላበት በማለቱ መቋረጡ ታውቋል።
ይህም ሆኖ ግን በአቶ በቀለ ገርባ፣በአቶ ደጀኔ ጣፋና አያና ጉርሜሳ የክስ ሒደት በመከላከያ ምስክርነት የተጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና አባዱላ ገመዳ እንዲሁም የኦሮሚያው ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በፌደራሉ ከፍተኝ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ባለፉት 25 አመታት ግን በፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዝዘው ሕግ አክብረው የተገኙ የሕወሃት/ኢህአዲግ ባለስልጣናት የሉም።
በ1997 ከነበረው የተጭበረበረ ምርጫ ጋር ተያይዞ በቅንጅት አመራሮች ተከሰው የነበሩት ሟቹ ጥቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዝዘው ሳይቀርቡ መቅረታቸው ይታወሳል።
እነዚህም ከፍተኛ ባለስልጣናት ሰበብ ፈልገው እንደሚቀሩና የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ያከብራሉ ተብሎ አይጠበቅም የሚሉ በርካታ ናቸው።
ለስሙ ግን ፍርድ ቤቱ 3ቱን ባለስልጣናት ከጥቅምት 27 እስከ ጥቅምት 29/2010 ባለው ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ 4ኛ ወንጀል ችሎት ትእዛዝ ሰጥቷል።