(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 11/2009) ማንኛውም ባለስልጣንም ሆነ የመንግስት ሰራተኛ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ሲወጣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መፈቀድ እንዳለበት መመሪያ ወጣ።
የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በሕዝብ ገንዘብ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን እንዳይዙ፣ ድል ያለ ድግስ እንዳይደግሱና ወጭአቸውን እንዲቆጥቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መመሪያ አውጥቷል።
ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከእንግዲህ አዲስ ቢሮ መከራየትም አይችሉም ተብሏል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው መመሪያ ማንኛውም ባልስልጣንም ሆነ የመንግስት ሰራተኛ ወደ ውጭ ሲወጣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መታወቅ አለበት።
ይህም መመሪያ ሰሞኑን ተጀመረ ከተባለው የሙስና ዘመቻ ጋር በተያያዛ ከሀገር እንዳይወጡ የታገዱትን ባለስልጣናት ስለመመልከቱ የተገለጸ ነገር የለም።
የኢሳት ምንጮች ሰሞኑን እንደገለጹት በደህንነት መስሪያ ቤቱ የተለዩና የታወቁ የሕወሃት ባለስልጣናት ሳይቀር በግላቸውም ቢሆን ከሐገር መውጣት አይችሉም።
በዚሁም ምክንያት ከአውሮፕላን ማረፊያ የተመለሱና ቪዛ ይዘውም ፈርተው የተቀመጡ እንዳሉ ነው የተነገረው።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የወጣውና በአዲስ መልክ ይፋ የተደረገው መመሪያ የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በህዝብ ገንዘብ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን መግዛት አይችሉም።
ከዚህ ቀደም በዞን ባለስልጣናት ሳይቀር ስለተገዙና ቅንጡ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ስለሚንዳላቀቁ የአገዛዙ የስራ ሃላፊዎችን የፖለቲካ ካድሬዎች ግን የተገለጸ ነገር የለም።
ይህ ብቻ አይደለም የመንግስት መስሪያ ቤቶች በሰበባሰበቡ መደገስ አይችሉም።የቀን መቁጠሪያ ካላንደር፣አጀንዳ፣መጽሔት፣የደስታ መግለጫ ካርድና ቲሸርት ማሳተምም አይችሉም ነው የተባለው።
ከዚህ ቀደም አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት በስማቸው ሳይቀር አጀንዳ ያሳትሙ እንደነበር ተነግሯል።
በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚደረጉ ስብሰባዎች ቦርሳ፣ቲሸርት፣ኮፍያ፣ሻርፕ፣የባህል ልብሶች መግዛትም አይቻልም ነው የተባለው።
ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ የአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚገኙባቸው ጉባኤዎች እነዚሁ ሕትመቶች ከፍተኛ የሙስና ምንጮች እንደሆኑ ይነገራል።
በዚህ ረገድ አንዳንድ የመንግስት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ሕዳሴ የሚሉና የባለስልጣናትን ስራዎች የሚያወድሱ መጽሔቶችን በማዘጋጀት ወደ ሚሊየነርነት የተሸጋገሩም እንዳሉ ይነገራል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች አዲስ ቢሮ መከራየትም ሆነ የቋሚ እቃ ግዥ ማካሄድ አይችሉም።
የሞባይል ካርድም ቢሆን ለከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣናት ካልሆነ በስተቀር ገዝቶ መሙላት ክልክል ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ይህን አዲስ መመሪያ ብዙ የሀገር ሀብት ከባከነ በኋላ ለምን በአሁኑ ጊዜ ማውጣት እንዳስፈለገው የተገለጸ ነገር የለም።
ብዙዎች ግን ሕዝባዊ አመጹ ያስከተለው ውጤት ሊሆን ይችላል ያላሉ።