(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 10/2009)በሶስት ሳምንት ብቻ 17 ኢትዮጵያውያን በመብረቅ ተመተው ሕይወታቸው አለፈ።
በርካታ እንስሳትም በአደጋው አልቀዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ደግሞ በህክምና ላይ ይገኛሉ።
የቻይናው ዜና አገልግሎት ዥንዋ እንደዘገበው የመብረቅ አደጋው የተከሰተው በኢትዮጵያ አፋር ክልል ነው።
የአፋር ክልላዊ መንግስት የፖሊስ ሃላፊ አሊ ቡቶ እንደተናገሩት ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በተከሰተው መብረቅ ባለፈው እሁድ ብቻ አራት ሰዎች ሲሞቱ፣በአጠቃላይ በሶስት ሳምንት ውስጥ በመብርቅ የሞቱት ሰዎች ቁጥርም 17 ድርሷል።
ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ደግሞ በህክምና ላይ ይገኛሉ።
ባለፈው ሰኔ በጀመረውና እስከ መስከረም በሚቀጥለው ክረምት ተጨማሪ የመብረቅ አደጋ ሊከሰት እንደሚችልና ከዚሁ ጋርም ተያይዞ የሰዎች ህይወት ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ የፖሊስ ሃላፊው ተናግረዋል።
በአለማችን በየአመቱ ከ20 ሺ የማያንሱ ሰዎች በመብረቅ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጥናቶች ያሳያሉ።
በዩ ኤስ አሜሪካ ብቻ ከ2006 እስከ 2014 ባሉት 8 አመታት 277 ሰዎች በመብረቅ ሕይወታቸውን አጥተዋል።