(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 8/2009) በኢትዮጵያ 16 የጥጥ እርሻ ልማት ድርጅቶች በአንድ የቱርክ ኩባንያ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ መጭበርበራቸውን አመለከቱ።
የጥጥ ልማት ድርጅቶቹ በደረቅ ቼክ የተጭበረበሩት ኤልሴ አዲስ በተባለ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ነው።
የቱርኩን ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኩባንያው ባለቤት 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብር ተበድሮ መጥፋቱን አስታውቋል።
ኢትዮጵያውያኑ የጥጥ አምራቾች በጠራራ ጸሃይ በኢንቨስትመንት ስም በመጣ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በደረቅ ቼክ ተጭበርብረናል ይላሉ።
ፋብሪካው የጥጥ ምርታቸውን ከገዛ በኋላ በምትኩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደረቅ ቼክ ሰጥቶአቸዋል።
ወደ ባንኩ ብሩን ለማምጣት ሲሄዱ ግን የተባለው ገንዘብ አለመኖሩ ተነግሯቸዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበኩሉ ኤልሴ አዲስ የተባለው የቱርክ ኩባንያ ባለቤት 1 ቢሊየን የሚጠጋ ብር ተበድሮ ከሀገር መሰወሩን ይፋ አድርጓል።
እናም ባንኩ ፋብሪካውን ወርሶ ለመሸጥ ቢሞክርም ገዢ ማጣቱን ነው የገለጸው።
በደረቅ ቼክ የተጭበረበሩት የጥጥ አምራች ባለቤቶች ልማት ባንክ ፋብሪካውን እያስተዳደረ ስለሆነ ገንዘባችን ሊከፈለን ይገባል ይላሉ።
ባንኩ ግን ፋብሪካው 800 ሚሊየን ቢሸጥ እንኳ ከቱርኩ ባለሃብት የምፈልገው 1መቶ ሚሊየን ብር ይቀረኛል በማለት የጥጥ አምራቾቹን ጥያቄ ለመመለስ እንደማይችል ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት ልማት ባንክ በብድር አመላለስ አሰራሩ ላይ በመያዣ ላይ ከመወሰን ይልቅ ክትትል ማድረግም ይኖርበታል።
ባለሃብቱ ገንዘብ ሳይኖረው ለምን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠው ለሚለው ግን ምላሽ አልሰጡም።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከቱርኩ ባለሃብት የባከነበት ገንዘብ እንዳለ ሆኖ በተያዘው የበጀት አመት የተበላሸ ብድር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የመንግስት ፋይናንስ ኤጀንሲ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ኤጀንሲው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ከ5 እስከ 10 በመቶ መብለጥ ባይኖርበትም 25 በመቶ መድረሱ እጅግ የሚያሳስብ ሆኗል።
የተበላሸ ብድር ከተባሉት ደግሞ ኢፈርትና የህወሃት ድርጅቶች ወስደው ያልመለሱት እንደሚበዛ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ።